10 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “ከአንተ ጋር ኪዳን እገባለሁ፤ ከዚህ ቀደም በዓለም ሁሉ ለየትኛውም ሕዝብ ከቶ ያልተደረገ፣ በሕዝብህ ሁሉ ፊት ድንቅ አደርጋለሁ፤ በመካከላቸው አብረሃቸው የምትኖር ሕዝብ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአንተ የማደርግልህ ሥራ የቱን ያህል አስፈሪ እንደሆነ ያያሉ።
11 ዛሬ የማዝህን ፈጽም፤ አሞራውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያውያንንና ኢያቡሳውያንን በፊትህ አስወጣቸዋለሁ።
12 ከምትሄድበት አገር ነዋሪዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ አለዚያ በመካከልህ ወጥመድ ይሆኑብሃል።
13 መሠዊያዎቻቸውን ሰባብሩ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን አድቅቁ፤ የአሼራ ዐፀዶቻቸውንም ቍረጡ።
14 ስሙ ቀናተኛ የሆነው እግዚአብሔር (ያህዌ) ቀናተኛ አምላክ (ኤሎሂም) ነውና ሌላ አምላክ አታምልክ።
15 “በምድሪቱ ከሚኖሩት ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ ምክንያቱም አምላኮቻቸውን ተከትለው ባመነዘሩና መሥዋዕትም ባቀረቡላቸው ጊዜ ይጋብዙሃል፤ አንተም መሥዋዕታቸውን ትበላለህ።
16 ለወንዶች ልጆችህም ሴቶች ልጆቻቸውን ስታጭላቸውና እነዚህም ሴቶች ልጆች አምላኮቻቸውን በመከተል ሲያመነዝሩ፣ ወንዶች ልጆችህን ተመሳሳይ ድርጊት እንዲፈጽሙ ያነሣሷቸዋል።