ዘፀአት 35:21-27 NASV

21 ፈቃደኛ የነበረና ልቡን ያነሣሣው ሁሉ በመምጣት ለመገናኛው ድንኳን ሥራ፣ ለአገልግሎቱ ሁሉና ለተቀደሱ ልብሶች የሚሆን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መባ አመጡ።

22 ፈቃደኛ የነበሩ ሁሉ፣ ወንዶችም ሴቶችም መጥተው ከሁሉም ዐይነት የወርቅ ጌጦች አመጡ የአፍንጫ ጌጦችን፣ ሎቲዎችን፣ ቀለበቶችን፣ ድሪዎችንና ጌጣጌጦችን ሁሉ አመጡ፤ ሁሉም ወርቃቸውን እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቀረቡ።

23 ሰማያዊ፣ ሐምራዊ ወይም ቀይ ማግ ወይም ቀጭን ሐር ወይም የፍየል ጠጒር፣ ቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ ወይም የአቆስጣ ቆዳ አመጡ።

24 የብር ወይም የናስ መባ ማቅረብ የቻሉ ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መባ አድርገው አመጡ፤ የግራር ዕንጨት ያለው ሁሉ አስፈላጊ በሆነው ሥራ እንዲውል አመጣው።

25 ጥበበኞች የሆኑ ሴቶች ሁሉ በእጃቸው ፈተሉ፤ የፈተሉትንም ሰማያዊ ሐምራዊ ወይም ቀይ ማግ ወይም ቀጭን በፍታ አመጡ።

26 ፈቃደኛ የነበሩና ጥበቡ ያላቸው ሴቶች ሁሉ የፍየል ጠጒር ፈተሉ።

27 መሪዎቹም ኤፉድና በደረት ኪሱ ላይ እንዲሆን የከበሩ ድንጋዮችንና ሌሎች ዕንቍዎች አመጡ።