ዘፀአት 35:29-35 NASV

29 ፈቃደኛ የሆኑ እስራኤላውያን ወንዶችና ሴቶች ሁሉ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ በኩል እንዲያከናውኑት ላዘዛቸው ሥራ ሁሉ የበጎ ፈቃድ ስጦታዎችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አመጡ።

30 ከዚያም ሙሴ እስራኤላውያንን አላቸው፤ “እነሆ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከይሁዳ ነገድ የሆነውን የሆር ልጅ፣ የኡሪን ልጅ ባስልኤልን መርጦአል።

31 በጥበብ፣ በችሎታና በዕውቀት፣ በማናቸውም ዐይነት ሙያ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) መንፈስ ሞልቶበታል፤

32 ይኸውም በወርቅ፣ በብርና በናስ የጥበብ ሥራ እንዲሠራ ነው፤

33 ድንጋዮችን እንዲጠርብና እንዲያወጣ፣ የዕንጨት ሥራ እንዲሠራና ማንኛውንም ዐይነት የጥበብ ሙያ እንዲያከናውን ነው።

34 እንዲሁም ለእርሱና ከዳን ነገድ ለሆነው ለአሂሳሚክ ልጅ ለኤልያብ፣ ለሁለቱም ሌሎችን የማስተማር ችሎታ ሰጣቸው።

35 የጥበብ ባለ ሙያዎች፣ ዕቅድ አውጭዎች፣ በሰማያዊ በሐምራዊና በቀይ ማግ፣ በቀጭን ሐር ጥልፍ ጠላፊዎችና ፈታዮች፤ ሁሉም ዋና የጥበብ ባለሙያዎችና ዕቅድ አውጭዎች በመሆን ማንኛውንም ዐይነት ሥራ ያከናውኑ ዘንድ በጥበብ ሞል ቶአቸዋል።