ዘፀአት
ምዕራፎች 36:4-10
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
4ስለዚህ የመቅደሱን ሥራ ሁሉ ይሠሩ የነበሩ ጥበበኞች የሆኑ ባለ ሙያዎች ሁሉ ሥራቸውን ትተው መጡ፤
5ሙሴንም፣ “ሕዝቡ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲሠራ ላዘዘው ሥራ ከበቂ በላይ እያመጡ ነው” አሉት።
6ከዚያም ሙሴ ትእዛዝ ሰጠ፤ ይህንንም ቃል ወደ ሰፈሩ ላኩት፤ “ማንም ወንድ ወይም ሴት ለመቅደሱ ሌላ ምንም ስጦታ ማድረግ የለበትም፤” ስለዚህ ሕዝቡ ትርፍ እንዳያመጡ ተከለከሉ፤
7ምክንያቱም ሥራውን ሁሉ ለማከናወን በእጃቸው ያለው ከበቂ በላይ ነበረ።
8የሥራ ችሎታ ካላቸው ሰዎች መካከል ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች ሁሉ የማደሪያውን ድንኳን በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታና ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ በጥልፍ ዐዋቂ፣ ኪሩቤል ከተጠለፉበት ከዐሥር መጋረጃዎች ሠሩት።
9መጋረጃዎቹም ሁሉ ተመሳሳይ መጠን ያላቸው ሲሆን፣ ቁመታቸው ሃያ ስምንት ክንድ፣ ወርዳቸው አራት ክንድ ነበር።
10አምስቱን መጋረጃዎች ባንድ ላይ በማጋጠም ሰፏቸው፤ የቀሩትን አምስቱንም እንዲሁ አደረጉ።