4 ለኤፉዱ ከሁለቱ ጐኖቹ ጋር ተያይዘው ያሉትን የትከሻ ንጣዮችን ሠሩ፤ ይኸውም ማያያዝ እንዲቻል ነው።
5 በጥበብ የተፈተለው መታጠቂያ በተመሳሳይ መልክ ሆኖ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው፣ ከኤፉዱ ጋር አንድ ወጥ የሆነና ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ በቀጭኑ ከተፈተለ ሐር የተሠራ ነበረ።
6 የከበሩ መረግዶችን በወርቅ ፈርጦች በመክፈፍ፣ እንደ ማኅተም የእስራኤልን ልጆች ስሞች ቀረጹባቸው።
7 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው በኤፉዱ የትከሻ ንጣዮች ላይ ለእስራኤል ልጆች እንደ መታሰቢያ ድንጋዮች አያያዟቸው።
8 የደረት ኪሱንም ጥበበኛ ባለ ሙያ እንደሚሠራው ሥራ በተመሳሳይ መንገድ ሠሩት፤ እንደ ኤፉዱም ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ በቀጭኑም ከተፈተለ በፍታ ሠሩት።
9 ርዝመቱ አንድ ስንዝር ወርዱም አንድ ስንዝር ሲሆን፣ ጥንድ ድርብ ሆኖ ባለ አራት ማእዘን ነበረ።
10 ከዚያም የከበሩ ድንጋዮችን በአራት ረድፍ በላዩ ላይ አደረጉበት፤ በመጀመሪያው ረድፍ ሰርድዮን፣ ቶጳዝዮንና የሚያብረቀርቅ ዕንቍ ነበር፤