ዘፀአት 4:13-19 NASV

13 ሙሴ ግን፣ “ጌታ ሆይ (አዶናይ)፤ እባክህ ሌላ ሰው ላክ” አለው።

14 በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቍጣ በሙሴ ላይ ነደደ፣ “ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደል? እርሱ ጥሩ እንደሚናገር ዐውቃለሁ፤ እንዲያውም አሁን ወደ አንተ እየመጣ ነው፤ በሚያይህም ጊዜ ከልቡ ደስ ይለዋል።

15 ለእርሱ ትነግረዋለህ፤ የሚናገራቸውንም ቃላት በአንደበቱ ታኖራለህ፤ ሁለታችሁም በትክክል እንድትናገሩ እረዳችኋለሁ፤ ምን ማድረግ እንዳለባችሁም አስተምራችኋለሁ።

16 አንተ እንደ አምላኩ ሆነህ ትነግረዋለህ፤ እርሱም እንደ አንደበትህ ሆኖ ለሕዝቡ ይናገርልሃል።

17 ታምራዊ ምልክት እንድታሳይባት ይህችን በትር በእጅህ ይዘህ ሂድ።”

18 ሙሴም ወደ አማቱ ወደ ዮቶር ተመልሶ ሄደና፣ “ወገኖቼ እስካሁን በሕይወት መኖራቸውን አይ ዘንድ ወደ ግብፅ ተመልሼ እንድሄድ እባክህ ፍቀድልኝ” አለው። ዮቶርም፣ “ሂድ፤ በሰላም ያግባህ” አለው።

19 ሙሴ በምድያም ሳለ እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “አንተን ሊገድሉህ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብፅ ሂድ” አለው።