24 ሙሴ በጒዞ ላይ በእንግዳ ማረፊያ ስፍራ ውስጥ ሳለ እግዚአብሔር (ያህዌ) አግኝቶት ሊገድለው ፈልጎ ነበር።
25 ሚስቱ ሲፓራ ግን ስለታም ባልጩት ወስዳ ልጇን ገረዘችው፤ በሸለፈቱ የሙሴን እግር በመንካትም “አንተ ለእኔ የደም ሙሽራዬ ነህ” አለችው።
26 ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ተወው፤ “አንተ የደም ሙሽራ ነህ” ያለችው በግርዛቱ ምክንያት ነው።
27 እግዚአብሔር (ያህዌ) አሮንን፣ “ሙሴን እንድታገኘው ወደ ምድረ በዳ ሂድ” አለው። እርሱም ሙሴን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ተራራ አገኘው፤ ሳመውም።
28 ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲናገር የላከውን ቃል በሙሉና እንዲፈጽማቸው ስላዘዘው ታምራዊ ምልክቶች ሁሉ ለአሮን ነገረው።
29 ሙሴና አሮን ሄዱና የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በአንድነት ሰበሰቡ፤
30 አሮንም እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ የነገረውን ቃል በሙሉ ነገራቸው። ታምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ።