ዘፀአት 7:15-21 NASV

15 ወደ ውሃው በሚሄድበት ጊዜ ማልደህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እንድታገኘውም በአባይ ዳር ተጠባበቅ፤ ወደ እባብ ተለውጣ የነበረችውንም በትር በእጅህ ያዝ።

16 ከዚያም እንዲህ በለው፤ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) “ሕዝቤ በምድረ በዳ ያመልኩኝ ዘንድ እንዲሄዱ ልቀቃቸው፤” ብዬ እንድነግርህ ላከኝ፤ አንተ ግን እስካሁን ድረስ እሺ አላልህም።

17 እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ “እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደሆንሁ በዚህ ታውቃለህ፤ እይ በዚህች በእጄ በያዝኳት በትር የአባይን ውሃ እመታለሁ። ወደ ደምም ይለወጣል።

18 በአባይ ወንዝ ውስጥ ያለው ዓሣ ይሞታል፤ ወንዙ ይከረፋል፤ ግብፃውያንም ውሃውን መጠጣት አይችሉም።’ ”

19 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “አሮንን፣ ‘በትርህን ውሰድና በግብፅ ውሆች ላይ፣ ይኸውም በምንጮች፣ በቦዮች፣ በኩሬዎችና በውሃ ማጠራቀሚያዎች ላይ እጅህን ዘርጋ’ ብለህ ንገረው፤ ወደ ደምም ይለወጣሉ። ከእንጨትና ከድንጋይ በተሠሩ ውሃ መያዣዎች ውስጥም ሳይቀር በግብፅ ምድር ደም በየቦታው ይሆናል።”

20 ሙሴና አሮን እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ አዘዛቸው አደረጉ። እርሱም በንጉሡና በሹማምንቱ ፊት በትሩን አንሥቶ የአባይን ወንዝ ውሃ መታ። ውሃውም በሙሉ ወደ ደም ተለወጠ።

21 በአባይ ያሉት ዓሦች ሞቱ፤ ወንዙም ከመከርፋቱ የተነሣ ግብፃውያኑ ውሃውን ሊጠጡት አልቻሉም። በግብፅ ምድር ሁሉ ደም ነበረ።