27 ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) እርሱ እንዳዘዘን መሥዋዕት ለመሠዋት ወደ ምድረ በዳ የሦስት ቀን መንገድ መሄድ አለብን።
28 ፈርዖንም፣ “ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በምድረ በዳ መሥዋዕት እንድ ትሠዉ እፈቅድላችኋለሁ፤ ነገር ግን ርቃችሁ እንዳትሄዱ። ለእኔም ጸልዩልኝ” አላቸው።
29 ሙሴም እንዲህ አለ፤ “ከአንተ እንደ ተለየሁ ወዲያውኑ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) እጸልያለሁ፤ ነገም ዝንቡ ሁሉ ከፈርዖን፣ ከሹማምቶቹና ከሕዝቡ ይወገዳል። ብቻ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት እንዲሠዉ ባለመፍቀድ ከዚህ ቀደም ፈርዖን አታሎ እንዳደረገው አሁንም እንዳያደርግ ርግጠኛ ይሁን።”
30 ከዚያም ሙሴ ከፈርዖን ተለይቶ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለየ።
31 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴ የለመነውን አደረገ። የዝንቡም መንጋ ከፈርዖን፣ ከሹማምቶቹና ከሕዝቡ ተወገደ፤ አንድም ዝንብ እንኳ አልቀረም።
32 በዚህም ጊዜ እንኳን ፈርዖን ልቡን አደነደነ እንጂ፣ ሕዝቡን አለቀቀም።