ዘፍጥረት 16:1-7 NASV

1 የአብራም ሚስት ሦራ፣ ልጆች አልወለደችለትም ነበር፤ እርሷም አጋር የምትባል ግብፃዊት አገልጋይ ነበረቻት።

2 አብራምንም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ልጅ እንዳልወልድ አድርጎኛል። ምናልባት በእርሷ በኩል ልጆች አገኝ እንደሆን ሄደህ ከአገልጋዬ ጋር ተኛ” አለችው።አብራምም ሦራ ባለችው ተስማማ።

3 አብራም በከነዓን ምድር ዐሥር ዓመት ከኖረ በኋላ ሚስቱ ሦራ ግብፃዊት አገልጋይዋን አጋርን ሚስት እንድትሆነው ለባሏ ሰጠችው።

4 አብራምም ከአጋር ጋር ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች። አጋርም ነፍሰ ጡር መሆኗን ባወቀች ጊዜ እመቤቷን መናቅ ጀመረች።

5 ሦራም አብራምን፣ “ለደረሰብኝ በደል ተጠያቂው አንተ ነህ፤ አገልጋዬ ዕቅፍህ ውስጥ እንድትገባ እኔው ሰጠሁህ፤ አሁን ግን ይኸው ማርገዟን ስታውቅ ትንቀኝ ጀመር፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በአንተና በእኔ መካከል ይፍረድ” አለችው።

6 አብራምም፣ “አገልጋይሽ እንደሆነች በእጅሽ ውስጥ ናት፤ የፈለግሽውን አድርጊባት” አላት። ከዚያም ሦራ ስላሠቃየቻት አጋር ጥላት ኰበለለች።

7 የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ አጋርን በአንድ የውሃ ምንጭ አጠገብ በምድረ በዳ አገኛት፤ ምንጩም ወደ ሱር በሚወስደው መንገድ ዳር ነበር።