ዘፍጥረት 20:2-8 NASV

2 በዚያም አብርሃም ሚስቱን ሣራን፣ “እህቴ ናት” ይል ነበር። ስለዚህ የጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክ መልእክተኛ ልኮ ሣራን ወሰዳት።

3 እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) በአንድ ሌሊት በሕልም ወደ አቢሜሌክ መጥቶ፣ “እነሆ፤ በወሰድሃት ሴት ምክንያት ምውት ነህ፤ እርሷ ባለ ባል ናት” አለው።

4 አቢሜሌክም ገና አልደረሰባትም ነበርና እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ በደል ያልፈጸመውን ሕዝብ ታጠፋለህን?

5 ‘እኅቴ ናት’ ያለኝ ራሱ አይደለምን? ደግሞስ ራሷም ብትሆን፣ ‘ወንድሜ ነው’ አላለችምን? እኔ ይህን ያደረግሁት በቅን ልቦናና በንጹሕ እጅ ነው።”

6 እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) በሕልሙ እንዲህ አለው፤ “አንተ ይህን ያደረግኸው በቅን ልቦና መሆኑን ዐውቄአለሁ፤ በእኔም ላይ ኀጢአት እንዳትሠራ የጠበቅሁህና እንዳትነካትም ያደረግሁት ለዚሁ ነው።

7 አሁንም ሚስቱን ለሰውዬው መልስለት፤ ነቢይ ነውና ይጸልይልሃል፤ አንተም ትድናለህ፤ ባትመልስለት ግን አንተም ሆንህ የአንተ የሆነ ሁሉ እንደምትሞቱ ዕወቅ።”

8 በማግስቱም ማለዳ፣ አቢሜሌክ ሹማምቱን ሁሉ ጠርቶ፣ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፤ እነርሱም ታላቅ ፍርሀት አደረባቸው።