ዘፍጥረት 22:3-9 NASV

3 በማግስቱ ጠዋት አብርሃም ማልዶ ተነሣ፤ አህያውን ጭኖ፣ ሁለት አገልጋዮቹንና ልጁን ይስሐቅን ይዞ፣ ለመሥዋዕት የሚበቃውን ዕንጨት ከቈረጠ በኋላ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወዳመለከተው ቦታ ለመሄድ ጒዞውን ጀመረ፤

4 በሦስተኛው ቀን አብርሃም ቀና ብሎ ቦታውን ከሩቅ ተመለከተ፤

5 አገልጋዮቹንም “እናንተ አህያውን ይዛችሁ እዚህ ቈዩን፤ እኔና ልጄ ግን ወደዚያ ሄደን ለእግዚአብሔር ሰግደን እንመለሳለን” አላቸው።

6 አብርሃም ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን ዕንጨት ወስዶ፣ ልጁን ይስሐቅን አሸከመው፤ እሳቱንና ቢላዋውንም ራሱ ያዘ። ሁለቱም አብረው ሄዱ።

7 ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን፣ “አባቴ ሆይ” አለው።አብርሃምም፣ “እነሆኝ፤ አለሁ ልጄ” አለው።ይስሐቅም፣ “እሳቱና ዕንጨቱ ይኸው፤ ነገር ግን የሚቃጠለው መሥዋዕት የት አለ?” ብሎ ጠየቀ።

8 አብርሃምም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለሚቃጠለው መሥዋዕት የሚሆነውን በግእግዚአብሔር ራሱ ያዘጋጃል (ኤሎሂም ይሬህሎ)” አለው። ሁለቱም አብረው ጒዞአቸውን ቀጠሉ።

9 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወዳመለከተው ቦታ እንደ ደረሱ፣ አብርሃም መሠዊያ ሠራ፤ በላዩም ላይ ዕንጨት ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው ዕንጨት ላይ አጋደመው።