ዘፍጥረት 22:7-13 NASV

7 ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን፣ “አባቴ ሆይ” አለው።አብርሃምም፣ “እነሆኝ፤ አለሁ ልጄ” አለው።ይስሐቅም፣ “እሳቱና ዕንጨቱ ይኸው፤ ነገር ግን የሚቃጠለው መሥዋዕት የት አለ?” ብሎ ጠየቀ።

8 አብርሃምም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለሚቃጠለው መሥዋዕት የሚሆነውን በግእግዚአብሔር ራሱ ያዘጋጃል (ኤሎሂም ይሬህሎ)” አለው። ሁለቱም አብረው ጒዞአቸውን ቀጠሉ።

9 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወዳመለከተው ቦታ እንደ ደረሱ፣ አብርሃም መሠዊያ ሠራ፤ በላዩም ላይ ዕንጨት ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው ዕንጨት ላይ አጋደመው።

10 ከዚያም ልጁን ለማረድ እጁን ዘርግቶ ቢላዋውን አነሣ።

11 የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ ግን ከሰማይ፣ “አብርሃም፤ አብርሃም፤” ብሎ ጠራው፤አብርሃምም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ።

12 እርሱም፣ “እጅህን በብላቴናው ላይ አታሳርፍ፤ ምንም ጒዳት አታድርስበት፤ እነሆ፤ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) እንደምትፈራ ተረድቻለሁ፤ ልጅህን፣ ያውም አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሳሳህምና” አለው።

13 አብርሃም ቀና ብሎ ሲመለከት በቊጥቋጦ መካከል ቀንዶቹ የተጠላለፉ አንድ አውራ በግ ከበስተ ኋላው አየ፤ ወደዚያው ሄዶ በጉን አመጣና የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው።