ዘፍጥረት 27:35-41 NASV

35 ይስሐቅም፣ “ወንድምህ መጥቶ አታሎኝ ምርቃትህን ወስዶብሃል” አለው።

36 ዔሳውም፣ “ይህ ሰው ያዕቆብ መባሉ ትክክል አይደለምን? እኔን ሲያታልለኝ ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው፤ መጀመሪያ ብኵርናዬን ወሰደብኝ፤ አሁን ደግሞ ምርቃቴን ቀማኝ” አለ። ቀጥሎም፣ “ታዲያ ለእኔ ያስቀረኸው ምንም ምርቃት የለም?” ብሎ ጠየቀ።

37 ይስሐቅም ለዔሳው፣ “በአንተ ላይ የበላይነት እንዲኖረው፣ ወንድሞቹ ሁሉ አገልጋዮቹ እንዲሆኑ፣ እህሉ፣ የወይን ጠጁም የተትረፈረፈ እንዲሆንለት መርቄዋለሁ። ታዲያ ልጄ፣ ለአንተ ምን ላደርግልህ እችላለሁ?” ሲል መለሰለት።

38 ዔሳውም አባቱን፣ “አባቴ ሆይ፤ ምርቃትህ ይህችው ብቻ ናትን? እባክህ አባቴ፣ እኔንም መርቀኝ” አለው፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ።

39 አባቱ ይስሐቅም እንዲህ ሲል መለሰለት፤“መኖሪያህከምድር በረከት፣ከላይም ከሰማይ ጠል የራቀ ይሆናል፤

40 በሰይፍ ትኖራለህ፤የወንድምህም አገልጋይ ትሆናለህ።አምርረህ በተነሣህ ጊዜ ግን፣ቀንበሩን ከጫንቃህ ላይ፣ወዲያ ትጥላለህ።”

41 አባቱ ያቆብን ስለ መረቀው፣ ዔሳው በያዕቆብ ላይ ቂም ያዘ፤ በልቡም፣ “ግድ የለም፤ የአባቴ መሞቻው ተቃርቦአል፤ ከልቅሶው በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድላለሁ” ብሎ አሰበ።