ዘፍጥረት 33:10-16 NASV

10 ያዕቆብም፣ “የለም፣ እንዲህ አይደለም፤ በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፣ እጅ መንሻዬን ተቀበል፤ በመልካም ሁኔታ ተቀብለኸኝ ፊትህን ማየት መቻሌ ራሱ፣ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ፊት የማየት ያህል እቈጥረዋለሁ።

11 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በቸርነቱ አሟልቶ ስለ ሰጠኝ የሚያስፈልገኝ ሁሉ አለኝና ያቀረብኹልህን እጅ መንሻ እባክህ ተቀበለኝ” አለው። ያዕቆብ አጥብቆ ስለ ለመነው፣ ዔሳው እጅ መንሻውን ተቀበለ።

12 ዔሳውም “በል ተነሥና ጒዟችንን እንቀጥል፤ እኔም እሄዳለሁ” አለው።

13 ያዕቆብ ግን እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ፣ እንደምታየው ልጆቹ ይህን ያህል የጠኑ አይደሉም፣ ለሚያጠቡት በጎችና ጥገቶች እንክብካቤ ማድረግ አለብኝ፤ እንስሳቱ ለአንዲት ቀን እንኳ በጥድፊያ ቢነዱ በሙሉ ያልቃሉ።

14 ስለዚህ ጌታዬ፣ አንተ ቀድመኸኝ ሂድ፤ እኔም በምነዳቸው እንስሳትና በልጆቹ ጒዞ ዐቅም ልክ እያዘገምሁ ሴይር ላይ እንገናኛለን።”

15 ዔሳው፣ “እንግዲያስ ከሰዎቼ ጥቂቶቹን ልተውልህ” አለው።ያዕቆብ ግን፣ “ለምን ብለህ? በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘቴ ብቻ ይበቃኛል” አለው።

16 ስለዚህ ዔሳው በዚሁ ዕለት ወደ ሴይር ለመመለስ ተነሣ።