22 ከወጣ በኋላም ሊያናግራቸው አልቻለም፤ በምልክት ከመጥቀስ በስተቀር መናገር ባለመቻሉ በቤተ መቅደስ ውስጥ ራእይ እንዳየ ተገነዘቡ።
23 ዘካርያስም የአገልግሎቱ ወቅት በተፈጸመ ጊዜ ወደ ቤቱ ተመለሰ።
24 ከዚህ በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ አምስት ወራትም ራሷን ሰወረች፤
25 እርሷም፣ “ጌታ በምሕረቱ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ሊያስወግድልኝ ተመልክቶ በዚህ ጊዜ ይህን አድርጎልኛል” አለች።
26 በስድስተኛው ወር፣ እግዚአብሔር መልአኩ ገብርኤልን በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ናዝሬት ከተማ ላከው፤
27 የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ።
28 መልአኩም እርሷ ወዳለችበት ገብቶ፣ “እጅግ የተወደድሽ ሆይ፤ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ የተባረክሽ ነሽ” አላት።