ሉቃስ 22 NASV

ይሁዳ ጌታን አሳልፎ ለመስጠት ተስማማ

1 በዚህ ጊዜ ፋሲካ የተባለው የቂጣ በዓል ተቃርቦ ነበር።

2 የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም ሕዝቡን ይፈሩ ስለ ነበር፣ እንዴት አድርገው ኢየሱስን እንደሚያስወግዱት መንገድ ይፈልጉ ነበር።

3 ሰይጣንም ከዐሥራ ሁለቱ ጋር በተቈጠረው የአስቆሮቱ ይሁዳ በተባለው ገባበት፤

4 ይሁዳም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ቤተ መቅደሱ ሹሞች ሄዶ ኢየሱስን እንዴት አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ተነጋገረ።

5 እነርሱም በዚህ ደስ ተሰኝተው፣ ገንዘብ ሊሰጡት ተዋዋሉ።

6 እርሱም በነገሩ ተስማማ፤ አሳልፎ ሊሰጣቸውም ሕዝብ የማይገኝበትን ምቹ ጊዜ ይጠብቅ ጀመር።

የመጨረሻው እራት

7 ከዚህ በኋላ የፋሲካ በግ የሚታረድበት የቂጣ በዓል ደረሰ።

8 ኢየሱስም፣ “የፋሲካን እራት እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን” ብሎ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላካቸው።

9 እነርሱም፣ “የት እንድናሰናዳ ትፈልጋለህ?” አሉት።

10 እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፤ ወደ ከተማ ስትገቡ የውሃ እንስራ የተሸከመ ሰው ያገኛችኋል፤ እርሱ ወደሚገባበት ቤት ድረስ ተከተሉት፤

11 ለቤቱም ባለቤት፣ ‘መምህሩ፣ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን እራት የምበላበት የእንግዳ ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል’ በሉት።

12 እርሱም በሰገነት ላይ ያለውን ተነጥፎ የተዘጋጀ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን።”

13 እነርሱም ሄደው ልክ ኢየሱስ እንደ ነገራቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካንም በዚያ አዘጋጁ።

14 ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር በማእድ ተቀመጠ፤

15 እንዲህም አላቸው፤ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ይህን ፋሲካ አብሬያችሁ ለመብላት በጣም ስመኝ ነበር፤

16 እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት የዚህ ትርጒም እስኪፈጸም ድረስ ይህን ፋሲካ ዳግመኛ አልበላም።”

17 ጽዋውን ተቀብሎ ካመሰገነ በኋላ እንዲህ አላቸው፤ “እንካችሁ፤ ሁላችሁ ከዚህ ተካፈሉ፤

18 እላችኋለሁና፤ ከአሁን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት እስከምትመጣ ድረስ፣ ከዚህ ወይን ፍሬ አልጠጣም።”

19 እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ፤ ቈርሶም ሰጣቸውና፣ “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ።

20 እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ፤ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚመሠረት አዲስ ኪዳን ነው።

21 ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ በማእድ ከእኔ ጋር ናት።

22 የሰው ልጅስ አስቀድሞ በተወሰነው መሠረት ይሄዳል፤ ነገር ግን እርሱን አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት።”

23 እነርሱም ከመካከላቸው ይህን የሚያደርግ ማን ሊሆን እንደሚችል እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር።

24 ደግሞም ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ በእነርሱ ዘንድ ክርክር ተነሣ።

25 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ ነገሥታት ሕዝቦቻቸውን በኀይል ይገዛሉ፤ በእነርሱ ላይ ሥልጣን ያላቸውም በጎ አድራጊዎች ተብለው ይጠራሉ።

26 በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይሁን፤ ይልቁን ከእናንተ ታላቅ የሆነ እንደ ታናሽ፣ ገዥ የሆነም እንደ አገልጋይ ይሁን።

27 ለመሆኑ፣ በማእድ ከተቀመጠና ቆሞ ከሚያስተናግድ ማን ይበልጣል? በማእድ የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ ያለሁት እንደ አንድ አገልጋይ ነው።

28 እናንተም ሳትለዩኝ በመከራዬ ጊዜ በአጠገቤ የቆማችሁ ናችሁ፤

29 አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም ደግሞ በመንግሥቴ እሾማችኋለሁ፤

30 ይኸውም በመንግሥቴ ከማእዴ እንድትበሉና እንድት ጠጡ ደግሞም በዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ እንድ ትፈርዱ ነው።”

31 ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ስምዖን፣ ስምዖን ሆይ፤ እነሆ፣ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤

32 እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ።”

33 ስምዖንም፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ ከአንተ ጋር ወህኒ ለመውረድም፣ ለመሞትም ዝግጁ ነኝ” አለው።

34 ኢየሱስም፣ “ጴጥሮስ ሆይ፤ ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ፣ አላውቀውም ብለህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እልሃለሁ” አለው።

35 ከዚያም ኢየሱስ፣ “ያለ ኰረጆ፣ ያለ ከረጢትና ያለ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” ብሎ ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “ምንም አልጐደለብንም” አሉ።

36 እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “አሁን ግን ኰረጆም፣ ከረጢትም ያለው ሰው ይያዝ፤ ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ይግዛ።

37 እላችኋለሁና፤ ‘ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ’ ተብሎ የተጻፈው በእኔ መፈጸም አለበት፤ ስለ እኔ የተጻፈው ፍጻሜው በርግጥ ደርሶአል።”

38 ደቀ መዛሙርቱም፣ “ጌታ ሆይ፤ እነሆ፤ ሁለት ሰይፎች እዚህ አሉ” አሉት።እርሱም፣ “ይበቃል” አላቸው።

ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ጸለየ

39 ኢየሱስ እንደ ልማዱ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።

40 እዚያም በደረሱ ጊዜ፣ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው።

41 ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ ያህል ርቆ ተንበርክኮ ጸለየ፤

42 እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፤ ፈቃድህ ከሆነ፣ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም።”

43 መልአክም ከሰማይ ተገልጦለት አበረታታው።

44 እጅግ ተጨንቆም በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ወደ ምድር ይፈስ ነበር።

45 ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ፤ እነርሱም ከሐዘን የተነሣ ተኝተው አገኛቸውና፣

46 “ለምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ” አላቸው።

ኢየሱስ ተያዘ

47 እርሱም ገና እየተነጋገረ ሳለ፣ ብዙ ሰዎች መጡ፤ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ የተባለውም ሰው ይመራቸው ነበር፤ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ተጠጋ።

48 ኢየሱስ ግን፣ “ይሁዳ ሆይ፤ የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው።

49 በኢየሱስ ዙሪያ የነበሩ ሰዎችም ሁኔታውን ተመልክተው “ጌታ ሆይ፤ በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉት።

50 ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው።

51 ኢየሱስ ግን፣ “ተው! እዚህ ድረስም ፍቀዱ” አለ፤ የሰውየውንም ጆሮ ዳሶ ፈወሰው።

52 ከዚያም ኢየሱስ ሊይዙት የመጡትን የካህናት አለቆች፣ የቤተ መቅደስ ሹሞችና ሽማግሌዎችን እንዲህ አላቸው፤ “ወንበዴ እንደሚይዝ ሰው፣ ሰይፍና ቈመጥ ይዛችሁ ወጣችሁን?

53 በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ከእናንተ ጋር በነበርሁ ጊዜ እጃችሁን አላነሣችሁብኝም፤ ይህ ግን ጨለማ የነገሠበት ጊዜያችሁ ነው።”

ጴጥሮስ ኢየሱስን ካደ

54 ከዚህ በኋላ ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት፤ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ አስገቡት፤ ጴጥሮስም በርቀት ይከተለው ነበር።

55 ሰዎቹ በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ እሳት አንድደው በአንድነት ተቀምጠው ሳለ፣ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ነበር።

56 አንዲት የቤት ሠራተኛም ጴጥሮስ እሳቱ አጠገብ ተቀምጦ አየችውና ትኵር ብላ በመመልከት፣ “ይህ ሰው ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ” አለች።

57 እርሱ ግን፣ “አንቺ ሴት፤ እኔ ዐላውቀውም” ብሎ ካደ።

58 ከጥቂት ጊዜ በኋላም አንድ ሌላ ሰው አይቶት፣ “አንተም ደግሞ ከእነርሱ አንዱ ነህ” አለው።ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፤ እኔ አይደለሁም” አለ።

59 አንድ ሰዓት ያህል ቈይቶም፣ ሌላ ሰው በርግጠኝነት፣ “ይህ ሰው ገሊላዊ ስለ ሆነ ያለ ጥርጥር ከእርሱ ጋር ነበረ” አለ።

60 ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፤ የምትለውን እኔ አላውቅም” አለ፤ ይህንም ተናግሮ ገና ሳይጨርስ ዶሮ ጮኸ።

61 ጌታም መለስ ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም፣ “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ ጌታ የተናገረው ቃል ትዝ አለው።

62 ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።

ወታደሮች በኢየሱስ ላይ አፌዙበት

63 ኢየሱስን አስረው ይጠብቁት የነበሩት ሰዎችም ያፌዙበትና ይመቱት ጀመር፤

64 ዐይኑንም ሸፍነው፣ “እስቲ ትንቢት ተናገር፤ የመታህ ማነው? እያሉ ይጠይቁት ነበር።

65 ሌላም ብዙ የስድብ ቃል እየተናገሩ ያቃልሉት ነበር።

ኢየሱስ በጲላጦስና በሄሮድስ ፊት

66 በነጋም ጊዜ፣ የሕዝብ ሽማግሌዎች፣ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስንም በሸንጎአቸው ፊት አቀረቡት።

67 እነርሱም፣ “አንተ ክርስቶስ ነህን? እስቲ ንገረን” አሉት።ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ብነግራችሁ አታምኑኝም፤

68 ብጠይቃችሁም አትመልሱም።

69 ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኀይል ቀኝ ይቀመጣል።”

70 በዚህ ጊዜ ሁሉም፣ “ታዲያ፣ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” አሉት።እርሱም፣ “መሆኔን እኮ እናንተው ተናገራችሁት” አላቸው።

71 እነርሱም፣ “ከእንግዲህ ሌላ ምስክር ምን ያስፈልገናል? ራሳችን ከገዛ አንደበቱ ሰምተናልና” አሉ።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24