ሉቃስ 1 NASV

መግቢያ

1 በእኛ መካከል ስለ ተፈጸሙት ነገሮች ብዙዎች ታሪኩን የተቻላቸውን ያህል ጽፈውት ይገኛል፤

2 ይህም ታሪክ ከመጀመሪያው አንሥቶ የዐይን ምስክሮችና የቃሉ አገልጋዮች የነበሩት ያስተላለፉልን ነው።

3 ክቡር ቴዎፍሎስ ሆይ፤ እኔም በበኩሌ ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ ከመረመርሁ በኋላ፣ ታሪኩን ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ፤

4 ይህንንም የማደርገው የተማርኸው ነገር እውነተኛ መሆኑን እንድታውቅ ነው።

የመጥምቁ ዮሐንስ መወለድ አስቀድሞ ተነገረ

5 በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን፣ ከአብያ የክህነት ምድብ የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱ ኤልሳቤጥም ከአሮን ነገድ ነበረች።

6 ሁለቱም የጌታን ትእዛዝና ሥርዐት ሁሉ ጠብቀው ያለ ነቀፋ የሚኖሩ፣ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤

7 ይሁን እንጂ ኤልሳቤጥ መካን በመሆኗ ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜ የገፉ ነበሩ።

8 አንድ ቀን ዘካርያስ በምድቡ ተራ፣ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት በሚያገለግልበት ጊዜ፣

9 በሥርዐተ ክህነቱ መሠረት፣ ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን በዕጣ ተመረጠ።

10 ዕጣን በሚታጠንበትም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ሆኖ ይጸልይ ነበር።

11 የጌታም መልአክ ከዕጣን መሠዊያው በስተ ቀኝ ቆሞ ታየው።

12 ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሀትም ተዋጠ።

13 መልአኩ ግን እንዲህ አለው፤ “ዘካርያስ ሆይ፤ አትፍራ፤ ጸሎትህ ተሰምቶአል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ።

14 በእርሱ ተድላና ደስታ ታገኛለህ፤ ብዙዎችም እርሱ በመወለዱ ደስ ይላቸዋል፤

15 በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና። የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ በእናቱም ማሕፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል።

16 ከእስራኤልም ሰዎች ብዙዎቹን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳቸዋል፤

17 የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው፣ የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ፣ ለጌታ የተገባ ሕዝብ ለማዘጋጀት በኤልያስ መንፈስና ኀይል በጌታ ፊት ይሄዳል።”

18 ዘካርያስም መልአኩን፣ “ይህን በምን አውቃለሁ? እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜ ገፍታለች” አለው።

19 መልአኩም መልሶ እንዲህ አለው፤ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህን እነግርህና ይህን የምሥራች አመጣልህ ዘንድ ተልኬአለሁ፤

20 እነሆ፤ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፣ይህም እስከሚፈጸምበት ቀን ድረስ ድዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም።”

21 በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ዘካርያስ ከቤተ መቅደሱ ሳይወጣ ለምን እንደ ዘገየ በመገረም ይጠባበቅ ነበር።

22 ከወጣ በኋላም ሊያናግራቸው አልቻለም፤ በምልክት ከመጥቀስ በስተቀር መናገር ባለመቻሉ በቤተ መቅደስ ውስጥ ራእይ እንዳየ ተገነዘቡ።

23 ዘካርያስም የአገልግሎቱ ወቅት በተፈጸመ ጊዜ ወደ ቤቱ ተመለሰ።

24 ከዚህ በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ አምስት ወራትም ራሷን ሰወረች፤

25 እርሷም፣ “ጌታ በምሕረቱ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ሊያስወግድልኝ ተመልክቶ በዚህ ጊዜ ይህን አድርጎልኛል” አለች።

የኢየሱስ መወለድ አስቀድሞ ተነገረ

26 በስድስተኛው ወር፣ እግዚአብሔር መልአኩ ገብርኤልን በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ናዝሬት ከተማ ላከው፤

27 የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ።

28 መልአኩም እርሷ ወዳለችበት ገብቶ፣ “እጅግ የተወደድሽ ሆይ፤ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ የተባረክሽ ነሽ” አላት።

29 ማርያምም በንግግሩ እጅግ በጣም ደን ግጣ፣ “ይህ ምን ዐይነት ሰላምታ ይሆን?” እያለች ነገሩን ታሰላስል ጀመር፤

30 መልአኩም እንዲህ አላት፤ “ማርያም ሆይ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ።

31 እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ።

32 እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤

33 በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።”

34 ማርያምም መልአኩን፣ “እኔ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው።

35 መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፤ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ የሚወለደው ቅዱሱ ሕፃን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።

36 እነሆ፤ ዘመድሽ ኤልሳቤጥም በስተ እርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መካን የተባለችውም ስድስተኛ ወሯን ይዛለች፤

37 ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።”

38 ማርያምም፣ “እነሆ፤ እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች። ከዚያም መልአኩ ተለይቶአት ሄደ።

ማርያም ኤልሳቤጥን ጥየቃ ሄደች

39 ማርያምም በዚያው ሰሞን በፍጥነት ተነሥታ ወደ ደጋው አገር፣ ወደ አንድ የይሁዳ ከተማ ሄደች፤

40 ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ አቀረበች።

41 ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ ፅንሱ በማሕፀኗ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤

42 ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፤ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው።

43 ለመሆኑ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ማን ነኝ?

44 እነሆ፤ የሰላምታሽ ድምፅ ጆሮዬ እንደ ገባ፣ በማሕፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሎአልና።

45 ጌታ ይፈጸማል ብሎ የነገራትን ያመነች እርሷ የተባረከች ናት!”

የማርያም መዝሙር

46 ማርያምም እንዲህ አለች፤“ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤

47 መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሰኛለች፤

48 እርሱ የባሪያውን መዋረድ ተመልክቶአልና።ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉብፅዕት ይሉኛል፤

49 ኀያል የሆነው እርሱ ታላቅነገር አድርጎልኛልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤

50 ምሕረቱም ለሚፈሩት ከትውልድእስከ ትውልድ ይኖራል።

51 በክንዱ ብርቱ ሥራ ሠርቶአል፤በልባቸው ሐሳብ የሚታበዩትን በትኖአቸዋል፤

52 ገዢዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአቸዋል፤ትሑታንን ግን ከፍ ከፍ አድርጎአቸዋል፤

53 የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአቸዋል፤ሀብታሞችን ግን ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል፤

54 ምሕረቱን በማስታወስ፣ ባሪያውንእስራኤልን ረድቶአል፤

55 ይህም ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፣ለአብርሃምና ለዘሩ ያለውን ለዘላለም ለመጠበቅ ነው።”

56 ማርያምም ሦስት ወር ያህል ኤልሳቤጥ ዘንድ ከቈየች በኋላ ወደ ቤቷ ተመለሰች።

የመጥምቁ ዮሐንስ መወለድ

57 የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ቀን ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች።

58 ጎረቤቶቿና ዘመ ዶቿም ጌታ ታላቅ ምሕረት እንዳደረገላት ሰሙ፤ የደስታዋም ተካፋዮች ሆኑ።

59 በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ሊሉት ፈለጉ፤

60 እናቱ ግን፣ “አይሆንም፤ ዮሐንስ መባል አለበት” አለች።

61 እነርሱም፣ “ከዘመዶችሽ በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም” አሏት።

62 አባቱንም ምን ስም ሊያወጣለት እንደሚፈልግ በምልክት ጠየቁት።

63 እርሱም መጻፊያ ሰሌዳ እንዲሰጡት ለምኖ፣ “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም በነገሩ ተደነቁ።

64 ወዲያውም አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱ ተፈታ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ መናገር ጀመረ።

65 ጎረቤቶቹም ሁሉ በፍርሀት ተሞሉ፤ ይህም ሁሉ ነገር በደጋማው የይሁዳ ምድር ሁሉ ተወራ።

66 ይህንም የሰሙ ሁሉ፣ “ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ ነገሩን በልባቸው ያዙ፤ የጌታ እጅ በርግጥ ከእርሱ ጋር ነበርና።

የዘካርያስ ትንቢት

67 የሕፃኑም አባት ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፤

68 “የእስራኤል አምላክ፣ ጌታ ይመስገን፤መጥቶ ሕዝቡን ተቤዥቶአልና።

69 በባሪያው በዳዊት ቤት፣የድነት ቀንድ አስነሥቶልናል፤

70 ይህም ጥንት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረው፣

71 ማዳኑም ከጠላቶቻችንና፣ከተፃራሪዎቻችን ሁሉ እጅ ነው፤

72 ይህንም ያደረገው ለአባቶቻችን ምሕረቱን ለማሳየት፣ቅዱስ ኪዳኑን ለማስታወስ፣

73 ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሐላ ለማሰብ፣

74 ከጠላቶቻችን እጅ አውጥቶ፣ያለ ፍርሀት እንድናገለግለው፣

75 በዘመናችንም ሁሉ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ ሊያቆመን ነው።

76 ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፤ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤የጌታን መንገድ ለማዘጋጀት በፊቱ ትሄዳለህና፤

77 የኀጢአታቸውን ስርየት ከማግኘታቸው የተነሣ፤ለሕዝቡ የመዳንን ዕውቀት ትሰጥ ዘንድ፣

78 ከአምላካችንም በጎ ምሕረት የተነሣ፣የንጋት ፀሓይ ከሰማይ ወጣችልን፤

79 ይኸውም በጨለማ ለሚኖሩት፣በሞት ጥላ ውስጥም ላሉት እንዲያበራና፣እግሮቻችንንም ወደ ሰላም መንገድ እንዲመራ ነው።”

80 ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤልም ሕዝብ በይፋ እስከታየበት ቀን ድረስ በበረሓ ኖረ።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24