1 በዚህ ጊዜ መጥተው፣ ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስለ ደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች ያወሩለት ሰዎች በዚያ ነበሩ።
2 እርሱም እንዲህ መለሰላቸው፤ “ታዲያ እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ሥቃይ የደረሰባቸው ከሌሎቹ የገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኀጢአተኞች ስለ ነበሩ ይመስላችኋል?
3 አይደለም እላችኋለሁ፤ ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ።
4 ወይም ደግሞ በሰሊሆም ግንብ ተንዶባቸው የሞቱት ዐሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ በደለኞች ስለ ነበሩ ይመስላችኋል?
5 አይደለም፤ እላችኋለሁ፤ ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ።”
6 ደግሞም እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ተናገረ፤ “አንድ ሰው በወይኑ ዕርሻ ቦታ የተተከለች አንዲት የበለስ ተክል ነበረችው፤ እርሱም ፍሬ ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም።
7 የወይን አትክልት ሠራተኛውንም፣ ‘እነሆ፤ ፍሬ ለማግኘት ልፈልግባት ሦስት ዓመት ወደዚህች በለስ መጥቼ ምንም አላገኘሁም፤ ስለዚህ ቍረጣት፤ ለምን ዐፈሩን በከንቱ ታሟጥጣለች?’ አለው።
8 “እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰለት፤ ‘ጌታ ሆይ፤ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፍግ እስከማደርግላት ድረስ ለዘንድሮ ብቻ ተዋት፤
9 ለከርሞ ካፈራች መልካም ነው፤ አለበለዚያ ትቈርጣታለህ።’ ”
10 ኢየሱስ በሰንበት ቀን በአንድ ምኵራብ ያስተምር ነበር።
11 በዚያም የድካም መንፈስ ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ አካለ ስንኩል ያደረጋት አንዲት ሴት ነበረች፤ እርሷም ከመጒበጧ የተነሣ ፈጽሞ ቀና ማለት አትችልም ነበር።
12 ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና፣ “አንቺ ሴት፤ ከሕመምሽ ነጻ ወጥ ተሻል” አላት፤
13 እጁንም በላይዋ ጫነ፤ እርሷም ወዲያው ቀጥ ብላ ቆመች፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነች።
14 የምኵራቡ አለቃ ግን፣ ኢየሱስ በሰንበት ቀን ስለ ፈወሰ ተቈጥቶ ሕዝቡን፣ “ሥራ ሊሠራባቸው የሚገባ ስድስት ቀኖች አሉ፤ ስለዚህ በእነዚያ ቀኖች እየመጣችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት ቀን አይደለም” አላ ቸው።
15 ጌታም መልሶ እንዲህ አለው፤ “እናንት ግብዞች፤ ከእናንተ መካከል አንድ ሰው በሬውን ወይም አህያውን በሰንበት ቀን ከማደሪያው ፈትቶ ውሃ ሊያጠጣ ይወስደው የለምን?
16 ታዲያ፣ ይህች ሴት የአብርሃም ልጅ ሆና ሳለች ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ በሰይጣን ታስራ ስትኖር፣ ከዚህ እስራት በሰንበት ቀን መፈታት አይገባትምን?”
17 ይህን በተናገረ ጊዜ ተቃዋሚዎቹ ሁሉ ዐፈሩ፤ ሕዝቡ ሁሉ ግን እርሱ ባደረገው ድንቅ ሥራ ሁሉ ደስ አላቸው።
18 ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት ምን ትመስላለች? ከምንስ ጋር ላመሳስላት?
19 አንድ ሰው ወስዶ በዕርሻው ውስጥ የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ አድጋ ዛፍ ሆነች፤ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎቿ ላይ ሰፈሩ።”
20 ደግሞም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር ላመሳስላት?
21 አንዲት ሴት ወስዳ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ በዛ ካለ ዱቄት ጋር የደባለቀችውን እርሾ ትመስላለች።”
22 ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እያመራ ሳለ፣ በሚያልፍባቸው ከተሞችና መንደሮች እያስተማረ ያልፍ ነበር።
23 አንድ ሰውም ቀርቦ፣ “ጌታ ሆይ፤ የሚድኑት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸውን?” አለው።እርሱም እንዲህ አላቸው፤
24 “በጠባቧ በር ለመግባት ተጣጣሩ፤ እላችኋለሁ፤ ብዙዎች ለመግባት ይፈልጋሉ ነገር ግን አይሆንላቸውም፤
25 የቤቱ ባለቤት ተነሥቶ በሩን ከቈለፈ በኋላ በውጭ ቆማችሁ፣ ጌታ ሆይ፤ ክፈትልን እያላችሁ በሩን ማንኳኳት ትጀምራላችሁ። “እርሱ ግን፣ ‘ማን እንደሆናችሁና ከየት እንደመጣችሁ አላውቅም’ ብሎ ይመልስላችኋል።
26 “እናንተም፣ ከአንተ ጋር አብረን በልተናል፤ ጠጥተናል፤ በአደባባያችንም አስተምረሃል ትላላችሁ።
27 “እርሱም፣ እላችኋለሁ፤ ‘ማን እንደሆናችሁና ከየት እንደመጣችሁ አላውቅም፤ እናንት ዐመፀኞች ሁሉ ከእኔ ራቁ’ ይላል።
28 “አብርሃምን፣ ይስሐቅንና ያዕቆብን፣ ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ስታዩ፣ እናንተ ግን ወደ ውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ በዚያን ጊዜ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
29 ሰዎች ከምሥራቅ፣ ከምዕራብ፣ ከሰሜንና ከደቡብ መጥተው በእግዚአብሔር መንግሥት በማእድ ይቀመጣሉ።
30 እነሆ፤ ከኋለኞች መካከል ፊተኞች የሚሆኑ፣ ከፊተኞች መካከልም ኋለኞች የሚሆኑ አሉ።”
31 በዚያን ጊዜ ከፈሪሳውያን አንዳንዶች መጥተው፣ “ሄሮድስ ሊገድልህ ስለሚፈልግ ተነሥተህ ከዚህ ሂድ” አሉት።
32 እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ሄዳችሁ ለዚያ ቀበሮ፣ እነሆ፤ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ፤ ሕመምተኞችን እፈውሳለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን ከግቤ እደርሳለሁ ብሎአል በሉት፤
33 ይሁን እንጂ ነቢይ ከኢየሩሳሌም ውጭ ይሞት ዘንድ አይገባምና ዛሬና ነገ፣ ከነገ ወዲያም ወደዚያው ጒዞዬን እቀጥላለሁ።
34 “ኢየሩሳሌም፣ ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ነቢያትን የምትገድዪ፣ ወደ አንቺ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግሪ! ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ፣ ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ፤ እናንተ ግን እምቢ አላችሁ፤
35 እነሆ፤ ቤታችሁ ወና ሆኖ ቀርቶአል። እላችኋለሁ፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ አታዩኝም።”