ሉቃስ 6 NASV

የሰንበት ጌታ

1 በአንድ የሰንበት ቀን ኢየሱስ በዕርሻ መካከል ያልፍ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም እሸት ቀጥፈው በእጃቸው እያሹ ይበሉ ነበር።

2 ከፈሪሳውያን መካከል አንዳንዶቹ ግን፣ “በሰንበት ቀን ሊደረግ ያልተፈቀደውን ለምን ታደርጋላችሁ?” አሏቸው።

3 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ዳዊት በተራበ ጊዜ ከባልንጀሮቹ ጋር ያደረገውን ከቶ አላነበባችሁምን?

4 ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ ለካህናት ብቻ የተፈቀደውን ኀብስተ ገጽ ወስዶ በላ፤ አብረውት ለነበሩትም ሰጣቸው።”

5 ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ለሰንበት ጌታዋ ነው” አላቸው።

6 በሌላ ሰንበት ቀንም ወደ ምኵራብ ገብቶ ያስተምር ነበር፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ አንድ ሰው ነበረ።

7 ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም ሊከሱት ምክንያት በመፈለግ፣ ይፈውሰው እንደሆነ ለማየት ይጠባበቁት ነበር።

8 ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እጁ የሰለለውን ሰው፣ “ተነሥተህ በመካካል ቁም” አለው፤ ሰውየውም ተነሥቶ ቆመ።

9 ኢየሱስም፣ “እስቲ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ፤ በሰንበት ቀን የተፈቀደው በጎ ማድረግ ነው ወይስ ክፉ ማድረግ? ነፍስ ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው።

10 ደግሞም ኢየሱስ በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየውም እንደ ተባለው አደረገ፤ እጁም ፈጽሞ ዳነለት።

11 ሰዎቹ ግን በቊጣ ተሞሉ፤ በኢየሱስ ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸውም እርስ በርስ ተወያዩ።

የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መመረጥ

12 ከእነዚያም ቀናት በአንዱ ኢየሱስ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ።

13 ሲነጋም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ ከእነርሱ ዐሥራ ሁለቱን መረጠ፤ እነዚህንም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤

14 እነርሱም፣ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ ፊልጶስ፣ በርተሎሜዎስ፣

15 ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ቀናተኛ የተባለው ስምዖን፤

16 የያዕቆብ ልጅ ይሁዳና ኋላ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነበሩ።

የቡራኬና የወዮታ ስብከት

17 ኢየሱስም አብሮአቸው ከተራራው ወርዶ ደልዳላ ቦታ ላይ ቆመ፤ ከደቀ መዛሙርቱም እጅግ ብዙ ሰዎች በዚያ ነበሩ፤ ከይሁዳ ሁሉና ከኢየሩሳሌም እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ጠረፍ የመጣ ብዙ ሕዝብም በዚያ ነበረ፣

18 እነዚህም የመጡት ሊሰሙትና ካለባቸው ደዌ ሊፈወሱ ነበር። በርኩሳን መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩትም ተፈወሱ፤

19 ኀይል ከእርሱ እየወጣ ሁሉንም ይፈውስ ስለ ነበር፣ ሰዎቹ ሁሉ እርሱን ለመንካት ይፈልጉ ነበር።

20 ወደ ደቀ መዛሙርቱም በመመልከት እንዲህ አለ፤ “እናንት ድኾች ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና፤

21 እናንት አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፤ ኋላ ትጠግባላችሁና፤ እናንት አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፤ ኋላ ትሥቃላችሁና፤

22 ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሏችሁ፣ ከመካከላቸው ሲለዩአችሁና ሲነቅፏችሁ፣ ክፉ ስምም ሲሰጧችሁ ብፁዓን ናችሁ።

23 “እነሆ፤ ወሮታችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፣ በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ፈንድቁም፤ የቀድሞ አባቶቻቸውም በነቢያት ላይ ያደረጉት ይህንኑ ነበርና።

24 “ነገር ግን እናንት ሀብታሞች ወዮላችሁ፤ መጽናናታችሁን አሁኑኑ ተቀብላችኋልና።

25 እናንት አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፤ ኋላ ትራባላችሁና። እናንት አሁን የምትሥቁ ወዮላችሁ፤ ኋላ ታዝናላችሁ፤ ታለቅሳላችሁም።

26 ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩላችሁ ወዮላችሁ፤ የቀድሞ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት ያደረጉላቸው ይህንኑ ነበርና።

ጠላትን መውደድ

27 “ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፤

28 የሚረግሟችሁን መርቁ፤ ለሚበድሏችሁም ጸልዩ።

29 አንዱን ጒንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጉንጭህን ደግሞ ስጠው፤ መጐናጸፊያህን ለሚወስድብህ እጀ ጠባብህን አትከልክለው።

30 ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፤ ንብረትህን የሚወስድ እንዲመልስልህ አትጠይቀው።

31 ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው።

32 “የሚወዷችሁን ብትወዱ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ የሚወዷቸውን ይወዳሉና።

33 መልካም ላደረጉላችሁ መልካም ብታደርጉ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ እንደዚያ ያደርጋሉና።

34 ብድር ይመልሳሉ ለምትሉት ብታበድሩ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ ያበደሩትን ያህል መልሰው ለመቀበል ‘ለኀጢአተኞች’ ያበድራሉ።

35 ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ መልሳችሁ ለመቀበል ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፤ በዚህም ወሮታችሁ ታላቅ ይሆናል፤ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ቸር ነውና።

36 አባታችሁ ርኅሩኅ እንደሆነ እናንተም ርኅሩኆች ሁኑ።

በሌሎች አለመፍረድ

37 “አትፍረዱ፤ አይፈረድባችሁም፤ አትኰንኑ፤ አትኰነኑም። ይቅር በሉ፤ ይቅር ትባላላችሁ።

38 ስጡ፤ ይሰጣችኋል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ስለሚሰፈርላችሁ፣ ጫን በተደረገ፣ በተነቀነቀና በተትረፈረፈ መልካም መስፈሪያ ተሰፍሮ በዕቅፋችሁ ይሰጣችኋል።”

39 ደግሞም ይህን ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱ ተያይዘው ጒድጓድ አይገቡምን?

40 ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ነገር ግን በሚገባ የተማረ ሰው ሁሉ እንደ መምህሩ ይሆናል።

41 “በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጒድፍ ለምን ታያለህ? በራስህ ዐይን ውስጥ የተጋደመውን ግንድ አትመለከትምን?

42 በራስህ ዐይን ውስጥ ያለውን ግንድ ሳታይ ወንድምህን፣ ‘ወንድሜ ሆይ፤ በዐይንህ ውስጥ ያለውን ጒድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ልትለው ትችላለህ? አንተ ግብዝ፤ በመጀመሪያ በዐይንህ ውስጥ የተጋደመውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያ በኋላ በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጒድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ።

ዛፍና ፍሬው

43 “መልካም ዛፍ ሆኖ ሳለ መጥፎ ፍሬ የሚያፈራ የለም፤ እንዲሁም መጥፎ ዛፍ ሆኖ መልካም ፍሬ የሚያፈራ የለም።

44 ዛፍ ሁሉ በፍሬው ይታወቃል፤ ከእሾኽ የበለስ ፍሬ አይለቀምም፤ ከቀጋ ቁጥቋጦ የወይን ፍሬ አይቈረጥም።

45 መልካም ሰው በልቡ ከሞላው መልካም ነገር መልካሙን ያወጣል፤ ክፉ ሰውም በልቡ ከሞላው ክፉ ነገር ክፉውን ያወጣል፤ ሰው በልቡ ሞልቶ የተረፈውን በአፉ ይናገራልና።

ልባምና ሰነፍ ቤተ ሠሪዎች

46 “እኔ የምለውን አታደርጉም፤ ታዲያ ለምን፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ’ ትሉኛላችሁ?

47 ወደ እኔ የሚመጣ፣ ቃሌንም ሰምቶ የሚፈጽም ሁሉ ማንን እንደሚመስል ላሳያችሁ፤

48 ቤት ለመሥራት አጥልቆ የቈፈረና በዐለት ላይ መሠረቱን የመሠረተ ሰው ይመስላል፤ ጐርፍ በመጣ ጊዜ የውሃው ሙላት ያን ቤት ገፋው፤ በሚገባ ስለ ታነጸም ሊያነቃንቀው አልቻለም።

49 ቃሌን ሰምቶ የማይፈጽም ግን ቤቱን ያለ መሠረት በዐፈር ላይ የሠራን ሰው ይመስላል፤ የወንዝ ሙላትም ቤቱን በመታው ጊዜ ወዲያው ወደቀ፤ ክፉኛም ፈራረሰ።”

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24