1 በዚያን ጊዜ፣ በብዙ ሺህ የሚቈጠር ሕዝብ እርስ በርስ እስኪረጋገጥ ድረስ ተሰብስቦ ሳለ፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ይል ጀመር፤ “ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠንቀቁ፤ ይህም ግብዝነት ነው።
2 የማይገለጥ የተሸፈነ፣ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለም።
3 ስለዚህ በጨለማ ያወራችሁት ሁሉ በብርሃን ይሰማል፤ በእልፍኝም ውስጥ በጆሮ ያንሾካሾካችሁት በሰገነት በይፋ ይነገራል።
4 “ወዳጆቼ ሆይ፤ እላችኋለሁ ሥጋን የሚገድሉትን፣ ከዚያ ወዲያ ግን ምንም ማድረግ የማይችሉትን አትፍሩ።
5 ነገር ግን መፍራት የሚገባችሁን አሳያችኋለሁ፤ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን እርሱን ፍሩት፤ አዎን፤ እርሱን ፍሩት እላችኋለሁ።
6 አምስት ድንቢጦች በዐሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ይሁን እንጂ ከእነርሱ አንዷ እንኳ በእግዚአብሔር ዘንድ አትዘነጋም።