3 ኢየሱስም ሕግ ዐዋቂዎችንና ፈሪሳውያንን፣ “በሰንበት ቀን ሕመምተኞችን መፈወስ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም?” ሲል ጠየቃቸው።
4 እነርሱ ግን ዝም አሉ። እርሱም ሰውየውን ይዞ ፈወሰውና አሰናበተው።
5 ደግሞም፣ “ከእናንተ አንዱ፣ ልጁ ወይም በሬው በሰንበት ቀን ጒድጓድ ቢገባበት ፈጥኖ የማያወጣው ማን ነው?” አላቸው።
6 እነርሱም ለዚህ አንዳች መልስ ሊያገኙ አልቻሉም።
7 ኢየሱስ ተጋባዦቹ የክብር ስፍራ ሲመርጡ ተመልክቶ፣ እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ለእነርሱ ነገራቸው፤
8 “አንድ ሰው ሰርግ ቢጠራህ፣ በክብር ስፍራ አትቀመጥ፤ በክብር ከአንተ የሚበልጥ ሰው ተጠርቶ ከሆነ፣
9 ሁለታችሁንም የጋበዘው መጥቶ፣ ስፍራውን ‘ለዚህ ሰው ልቀቅለት’ ይልሃል፤ አንተም እያፈርህ ወደ ዝቅተኛው ስፍራ ትሄዳለህ።