36 ደግሞም ከአሴር ወገን የሆነች የፋኑኤል ልጅ፣ ሐና የምትባል ነቢይት በዚያ ነበረች፤ እርሷም በጣም አርጅታ ነበር፤ በድንግልናዋ ካገባችው ባሏም ጋር ሰባት ዓመት የኖረች ነበረች፤
37 ዕድሜዋም ሰማንያ አራት ዓመት እስኪሆናት ድረስ ቀንና ሌሊት ከቤተ መቅደስ ሳትለይ፣ በጾምና በጸሎት የምታገለግል መበለት ሆና ቈየች።
38 በዚያኑም ጊዜ ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም መቤዠት ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ ሕፃኑ ተናገረች።
39 ዮሴፍና ማርያም በጌታ ሕግ የታዘዘውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ፣ በገሊላ አውራጃ ወዳለችው ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ።
40 ሕፃኑም እያደገና እየጠነከረ ሄደ፤ በጥበብ ተሞላ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ።
41 ወላጆቹም በየዓመቱ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር።
42 ልጁም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ፣ እንደተለመደው ወደ በዓሉ ወጡ።