ሉቃስ 5:10-16 NASV

10 ደግሞም የስምዖን ባልንጀሮች የነበሩት የዘብዴዎስ ልጆች፣ ያዕቆብና ዮሐንስም ተደነቁ።ኢየሱስም ስምዖንን፣ “አትፍራ፤ ከእንግዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” አለው።

11 እነርሱም ጀልባዎቹን ወደ ምድር ካስጠጉ በኋላ ሁሉን ትተው ተከተሉት።

12 ኢየሱስ ከከተሞች በአንዱ በነበረበት ጊዜ፣ አንድ ለምጽ የወረሰው ሰው በዚያው ከተማ ነበር፤ ይህ ሰው ኢየሱስን ባየው ጊዜ በፊቱ ተደፋና፣ “ጌታ ሆይ፤ ብትፈቅድ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” ብሎ ለመነው።

13 ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፣ “እፈቅዳለሁ፤ ንጻ!” አለው፤ ወዲያውም ለምጹ ጠፋለት።

14 ኢየሱስም፣ “ይህን ለማንም አትናገር፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ለእነርሱ ምስክር እንዲሆንም ስለ መንጻትህ ሙሴ ያዘዘውን መሥዋዕት አቅርብ” ሲል አዘዘው።

15 ይሁን እንጂ ስለ እርሱ የሚወራው ወሬ ይበልጥ እየሰፋ ሄደ፤ እጅግ ብዙ ሰዎችም እርሱ የሚናገረውን ለመስማትና ካለባቸው ደዌ ለመፈወስ ይሰበሰቡ ነበር።

16 ኢየሱስ ግን ብዙ ጊዜ ወደ ገለልተኛ ስፍራ ወጥቶ ይጸልይ ነበር።