16 ኢየሱስ ግን ብዙ ጊዜ ወደ ገለልተኛ ስፍራ ወጥቶ ይጸልይ ነበር።
17 አንድ ቀን ኢየሱስ እያስተማረ ነበር፤ በዚያም ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮች ሁሉ እንዲሁም ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ተቀምጠው ነበር፤ ይፈውስም ዘንድ የጌታ ኀይል ከእርሱ ጋር ነበረ።
18 በዚያን ጊዜም፣ ሰዎች አንድ ሽባ በዐልጋ ተሸክመው አመጡ፤ ኢየሱስ ፊት ለማኖርም ወደ ቤት ሊያስገቡት ሞከሩ፤
19 ከሕዝቡም ብዛት የተነሣ ቤቱ ውስጥ ማስገባት ስላቃታቸው፣ ጣራው ላይ ወጥተው የቤቱን ክዳን በመንደል በሽተኛውን ከነዐልጋው በሕዝቡ መካካል ቀጥታ ኢየሱስ ፊት አወረዱት።
20 ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ፣ “አንተ ሰው፤ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው።
21 ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም፣ “ይህ አምላክን በመዳፈር እንዲህ የሚናገር ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ኀጢአትን ሊያስተስረይ ማን ይችላል?” ብለው ያስቡ ጀመር።
22 ኢየሱስም ሐሳባቸውን ስለ ተረዳ እንዲህ አላቸው፤ “ለምን በልባችሁ እንዲህ ታስባላችሁ?