ሉቃስ 9:11-17 NASV

11 ሕዝቡም ይህንኑ ዐውቀው ተከተሉት፤ እርሱም ተቀብሎአቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፤ ፈውስ የሚያስፈልጋቸውንም ፈወሳቸው።

12 ቀኑም ሊመሽ ሲል፣ ዐሥራ ሁለቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ያለ ነው በምድረ በዳ ስለ ሆነ፣ ሕዝቡ ወደ አካባቢው መንደርና ገጠር ሄደው ማደሪያና ምግብ እንዲፈልጉ አሰናብታቸው” አሉት።

13 እርሱ ግን፣ “የሚበሉትን እናንተው ስጧቸው” አላቸው።እነርሱም፣ “ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚበቃ ምግብ ሄደን ካልገዛን በስተቀር፣ እኛ ያለን ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ አይበልጥም” አሉት፤

14 አምስት ሺህ ያህል ወንዶች በዚያ ነበሩና።ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሕዝቡን በአምሳ በአምሳ ሰው መድባችሁ አስቀምጧቸው” አላቸው።

15 ደቀ መዛሙርቱም በታዘዙት መሠረት ሰዎቹ እንዲቀመጡ አደረጉ።

16 እርሱም አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ እያየ ባረካቸው፤ ቈርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ።

17 ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ከእነርሱ የተረፈውን ቊርስራሽ እንጀራ ዐሥራ ሁለት መሶብ አነሡ።