ራእይ 21:17-23 NASV

17 ደግሞም የከተማዪቱን ቅጥር ለካ፤ ርዝመቱም የመልአክ መለኪያ በሆነው በሰው መለኪያ መቶ አርባ አራት ክንድ ነበር።

18 ቅጥሩ የተሠራው ከኢያሰጲድ ነበር፤ ከተማዪቱም እንደ መስተዋት ንጹሕ ከሆነ ወርቅ የተሠራች ነበረች።

19 የከተማዪቱ ቅጥር መሠረቶች በሁሉም ዐይነት የከበረ ድንጋይ ያጌጡ ነበር፤ የመጀመሪያው መሠረት ኢያሰጲድ፣ ሁለተኛው ሰንፔር፣ ሦስተኛው ኬልቄዶን፣ አራተኛው መረግድ፣

20 አምስተኛው ሰርዶንክስ፣ ስድስተኛው ሰርድዮን፣ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፣ ስምንተኛው ቢረሌ፣ ዘጠነኛው ወራውሬ፣ ዐሥረኛው ክርስጵ ራስስ፣ ዐሥራ አንደኛው ያክንት፣ ዐሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ።

21 ዐሥራ ሁለቱም በሮች ዐሥራ ሁለት ዕንቈች ነበሩ፤ እያንዳንዱም በር ከአንድ ዕንቍ የተሠራ ነበረ። የከተማዪቱም አውራ መንገድ እንደ መስተዋት ብርሃን የሚያስተላልፍ ንጹሕ ወርቅ ነበረ።

22 ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክና በጉ መቅደሷ ስለሆኑ፣ በከተማዪቱ ውስጥ ቤተ መቅደስ አላየሁም።

23 የእግዚአብሔር ክብር ብርሃን ስለሚሰጣትና በጉም መብራቷ ስለ ሆነ፣ ከተማዋ ፀሓይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጋትም።