11 ወደ ኢያቡስ እንደ ቀረቡም ጊዜው እየመሸ ስለ ነበር አገልጋዩ ጌታውን፣ “እንግዲህ ወደዚህች ወደ ኢያቡሳውያን ከተማ ጐራ ብለን እንደር” አለው።
12 ጌታውም፣ “አይሆንም፤ ሕዝቧ እስራኤላዊ ወዳልሆነ ወደ ባዕድ ከተማ አንገባም፤ ወደ ጊብዓ አልፈን እንሂድ” አለው።
13 ቀጥሎም፣ “በል ና፤ ወደ ጊብዓ ወይም ወደ ራማ ለመድረስ እንሞክርና ከዚያ በአንዱ ስፍራ እናድራለን” አለው።
14 ስለዚህም መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ የብንያም ነገድ ወደሆነችው ወደ ጊብዓ እንደ ደረሱም ፀሓይ ጠለቀች።
15 ለማደርም ወደዚያው ጎራ አሉ፤ ሄደውም በከተማዪቱ አደባባይ ተቀመጡ፤ ሆኖም በቤቱ ለማሳደር ማንም አልተቀበላቸውም ነበር።
16 በዚያች ምሽት ከኰረብታማው ከኤፍሬም አገር መጥቶ በጊብዓ የሚኖር አንድ መጻተኛ ሽማግሌ ከዕርሻ ሥራው መጣ፤ የዚያ አገር ሰዎች ግን ብንያማውያን ነበሩ።
17 ሽማግሌው ቀና ብሎ መንገደኛውን በከተማዪቱ አደባባይ ላይ ባየው ጊዜ፣ “ከወዴት መጣህ? ወዴትስ ትሄዳለህ?” ሲል ጠየቀው።