24 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
25 “አሮንንና ልጆቹን እንዲህ በላቸው፤ ስለ ኀጢአት መሥዋዕት አቀራረብ የምትከተለው ሥርዐት ይህ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኀጢአቱም መሥዋዕት እዚያው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይታረድ፤ ይህም እጅግ ቅዱስ ነው።
26 መሥዋዕቱንም የሚያቀርበው ካህን ይብላው፤ ይህም በተቀደሰው ስፍራ በመገናኛው ድንኳን ቅጥር ግቢ ውስጥ፣ በአደባባዩ ላይ ይበላ።
27 ሥጋውን የሚነካ ሁሉ የተቀደሰ ይሆናል፤ ደሙ በልብስ ላይ ቢረጭ፣ ያንልብስ በተቀደሰ ስፍራ እጠብ።
28 ሥጋው የተቀቀለበት የሸክላ ዕቃ ይሰበር፤ የናስ ዕቃ ከሆነ ግን ተፈግፍጎ በውሃ ይታጠብ።
29 ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ከዚህ መብላት ይችላል፤ ይህም እጅግ ቅዱስ ነው።
30 ነገር ግን ደሙ ለማስተስረያ እንዲሆን ወደ መገናኛው ድንኳን ወደ ቅድስት የቀረበው የኀጢአት መሥዋዕት ሁሉ በእሳት ይቃጠል እንጂ አይበላ።