ዘሌዋውያን 14 NASV

ከተላላፊ የቈዳ በሽታ የመንጻት ሥርዐት

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

2 “የታመመው ሰው እንዲነጻ ወደ ካህኑ በሚወስዱት ጊዜ ሥርዐቱ እንዲህ ነው፦

3 ካህኑ ከሰፈር ወደ ውጭ ወጥቶ ይመርምረው፤ ሰውየው ከተላላፊ የቈዳ በሽታው ተፈውሶ ከሆነ፣

4 ካህኑ ስለሚነጻው ሰው፣ ለመብላት ከተፈቀደው የወፍ ዐይነት ሁለት ከነሕይወታቸው፣ የዝግባ ዕንጨት፣ ደመቅ ያለ ቀይ ድርና ሂሶጵ እንዲያመጣ ይዘዝ።

5 ካህኑም ከወፎቹ አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ ባለ የምንጭ ውሃ ላይ እንዲታረድ ይዘዝ።

6 በሕይወት ያለውንም ወፍ ከዝግባው ዕንጨት፣ ደመቅ ካለው ቀይ ድርና ከሂሶጵ ጋር በምንጩ ውሃ ላይ በታረደው ወፍ ደም ውስጥ ይንከር።

7 ከተላላፊ በሽታ የሚነጻውንም ሰው ሰባት ጊዜ ይርጨው፤ መንጻቱንም ያስታውቅ፤ በሕይወት ያለውንም ወፍ ወደ ውጭ ይልቀቀው።

8 “የሚነጻው ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ጠጒሩን በሙሉ ይላጭ፤ ሰውነቱን በውሃ ይታጠብ፤ በሥርዐቱም መሠረት ንጹሕ ይሆናል። ከዚህም በኋላ ወደ ሰፈር መግባት ይችላል፤ ነገር ግን ሰባት ቀን ከድንኳኑ ውጭ ይቈይ።

9 በሰባተኛውም ቀን ጠጒሩን በሙሉ ይላጭ፤ ራሱን፣ ጢሙን፣ ቅንድቡንና ሌላውንም ጠጒር ሁሉ ይላጭ። ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱን በውሃ ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል።

10 “በስምንተኛው ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና ነውር የሌለባትን አንዲት የዓመት እንስት በግ ያቅርብ፤ እንዲሁም ለእህል ቊርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ የላመ ዱቄት ያቅርብ፤ ደግሞ አንድ ሎግ ዘይት ያምጣ።

11 ሰውየው የነጻ መሆኑን የሚያስታውቀው ካህን የሚነጻውን ሰውና መሥዋዕቶቹን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርብ።

12 “ካህኑም ከተባዕቱ ጠቦቶች በመውሰድ ከሎግ ዘይቱ ጋር የበደል መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ፤ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዝውዛቸው።

13 ጠቦቱንም፣ የኀጢአት መሥዋዕትና የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት በተቀደሰው ስፍራ ይረደው፤ የኀጢአት መሥዋዕቱ ለካህኑ እንደሚሰጥ ሁሉ የበደል መሥዋዕቱም ለካህኑ ይሰጥ፤ ይህም እጅግ የተቀደሰ ነው።

14 ካህኑ ከበደል መሥዋዕቱ ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ታችኛውን ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ያስነካ።

15 ካህኑም ከሎግ ዘይት ወስዶ በራሱ ግራ እጅ መዳፍ ውስጥ ይጨምር፤

16 የቀኝ እጁንም ጣት በመዳፉ በያዘው ዘይት ውስጥ በመንከር በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይርጭ።

17 ካህኑ በመዳፉ ውስጥ ከቀረው ዘይት ጥቂቱን ወስዶ የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ታችኛውን ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት በበደል መሥዋዕቱ ደም ላይ ደርቦ ይቅባ።

18 በመዳፉ ላይ የቀረውንም ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያድርግ፤ በእግዚአብሔርም (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለት።

19 “ካህኑም የኀጢአት መሥዋዕቱን ያቅርብ፤ ከርኵሰቱ ለሚነጻውም ሰው ያስተሰርይለት፤ ከዚህ በኋላ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ይረድ፤

20 ከእህል ቊርባኑም ጋር በመሠዊያው ላይ በማቅረብ ያስተሰርይለት፤ ሰውየውም ንጹሕ ይሆናል።

21 “ሰውየው ድኻ ከሆነና እነዚህን ለማቅረብ ዐቅሙ ካልፈቀደለት፣ ማስተሰረያ እንዲሆነው የሚወዘወዝ አንድ ተባዕት የበግ ጠቦት ለበደል መሥዋዕት፣ በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ የላመ ዱቄት ለእህል ቊርባን ያቅርብ፤ ደግሞም አንድ ሎግ ዘይት ያምጣ፤

22 እንዲሁም ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች ዐቅሙ የፈቀደውን አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ።

23 “እነዚህንም በስምንተኛው ቀን ስለ መንጻቱ ሥርዐት ወደ ካህኑ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርብ።

24 ካህኑም ለበደል መሥዋዕት የሚሆነውን የበግ ጠቦትና አንድ ሎግ ዘይት ይቀበል፤ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዝውዛቸው።

25 ለበደል መሥዋዕት የሚሆነውንም የበግ ጠቦት ይረድ፤ ከደሙም ጥቂት ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮ ታችኛ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ያስነካ፤

26 ከዘይቱም ጥቂቱን በግራ እጁ መዳፍ ውስጥ ያፍስስ፤

27 የቀኝ እጁንም ጣት በመዳፉ በያዘው ዘይት ውስጥ በመንከር በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ሰባት ጊዜ ይርጭ።

28 በመዳፉ ከያዘው ዘይት ጥቂቱን ወስዶ የበደል መሥዋዕቱን ደም ባስነካበት ቦታ፣ ይኸውም የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ያስነካ።

29 ካህኑ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለት ዘንድ በመዳፉ ከያዘው ዘይት የቀረውን በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያፍስ፤

30 ካህኑም ርግቦቹን ወይም የዋኖሶቹን ጫጩቶች የሰውየው ዐቅም የፈቀደውን ይሠዋል፤

31 ከእነዚህም አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ከእህሉ ቊርባን ጋር ያቅርብ፤ በዚህም ሁኔታ ካህኑ ለሚነጻው ሰው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለታል።”

32 ተላላፊ የቈዳ በሽታ ይዞት የሚነጻበትን መደበኛ መሥዋዕት ለማቅረብ ዐቅም ላነሠው ሰው ሕጉ ይህ ነው።

ልብስ ላይ ከሚታይ ተላላፊ በሽታ መንጻት

33 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤

34 “ርስት አድርጌ ወደምሰጣቸው ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፣ በዚያ አገር አንዱን ቤት በተላላፊ በሽታ የበከልሁ እንደሆነ፣

35 ባለቤቱ ወደ ካህኑ ሄዶ፣ ‘በቤቴ ውስጥ ተላላፊ በሽታ የሚመስል ነገር አይቻለሁ’ ብሎ ይንገረው።

36 ካህኑ ወደዚያ ቤት በመግባት በሽታውን መርምሮ ርኩስ መሆኑን ከማስታወቁ በፊት፣ ቤቱን ባዶ እንዲያደርጉት ይዘዝ፤ ከዚህ በኋላ ካህኑ ወደ ቤቱ ገብቶ ይመርምር።

37 በግድግዳው ላይ ያለውን ተላላፊ በሽታ በሚመረምርበት ጊዜ፣ መልኩ ወደ አረንጓዴነት ወይም ወደ ቀይነት የሚያደላ የተቦረቦረ ነገር በግድግዳው ቢታይ፣

38 ካህኑ ከቤቱ ወደ ደጅ ወጥቶ ቤቱን ሰባት ቀን ይዝጋው።

39 ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቤቱን ለመመርመር ይመለስ፤ ተላላፊው በሽታ በግድግዳው ተስፋፍቶ ቢገኝ፣

40 የተበከሉት ድንጋዮች ተሰርስረው እንዲወጡና ከከተማው ውጭ ባለው ርኩስ ስፍራ እንዲጣሉ ይዘዝ፤

41 የቤቱ ግድግዳ በሙሉ በውስጥ በኩል እንዲፋቅና ፍቅፋቂው ከከተማው ውጭ ባለው ርኩስ ስፍራ እንዲደፋ ያድርግ።

42 በወጡትም ድንጋዮች ቦታ ሌሎች ድንጋዮች አምጥተው ይተኩ፤ ሌላም ጭቃ ወስደው ቤቱን ይምረጉ።

43 “ድንጋዮቹ ወጥተው፣ ቤቱ ከተፈቀፈቀና ከተመረገ በኋላ ተላላፊው በሽታ እንደ ገና በቤቱ ውስጥ ከታየ፣

44 ካህኑ ሄዶ ይመርምረው፤ ተላላፊው በሽታ በቤቱ ውስጥ ተስፋፍቶ ከተገኘ፣ አደገኛ በሽታ ነው፤ ቤቱም ርኩስ ነው።

45 ስለዚህ ቤቱ ይፍረስ፤ ድንጋዩ፣ ዕንጨቱና ምርጊቱ በሙሉ ከከተማ ውጭ ባለው ርኩስ ስፍራ ይጣል።

46 “ቤቱ ተዘግቶ ሳለ ማንኛውም ሰው ቢገባበት፣ ያ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

47 በዚያ ቤት ገብቶ የተኛ ወይም የበላ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ይጠብ።

48 “ነገር ግን ቤቱ ከተመረገ በኋላ ካህኑ ሊመረምረው በሚመጣበት ጊዜ ተላላፊው በሽታ ሳይስፋፋ ቢገኝ፣ በሽታው ስለለቀቀው ቤቱ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ።

49 ቤቱንም ለማንጻት ሁለት ወፎች፣ የዝግባ ዕንጨት፣ ደመቅ ያለ ቀይ ድርና ሂሶጵ ያቅርብ።

50 ከወፎቹም አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ ባለ የምንጭ ውሃ ላይ ይረድ።

51 የዝግባውን ዕንጨት፣ ሂሶጱን፣ ደመቅ ያለውን ቀይ ድርና በሕይወት ያለውን ወፍ ወስዶ በታረደው ወፍ ደምና በምንጩ ውሃ ውስጥ ይንከር፤ ቤቱንም ሰባት ጊዜ ይርጭ።

52 ቤቱንም በወፉ ደም፣ በምንጩ ውሃ፣ በሕይወት ባለው ወፍ፣ በዝግባው ዕንጨት፣ በሂሶጱና ደመቅ ባለው ቀይ ድር ያንጻው።

53 በሕይወት ያለውንም ወፍ ከከተማ ወደ ውጭ ይልቀቀው፤ በዚህ ሁኔታ ለቤቱ ያስተሰርይለታል፤ ቤቱም ንጹሕ ይሆናል።”

54 ይህ ሕግ ለማንኛውም ተላላፊ የቈዳ በሽታ፣ ለሚያሳክክ ሕመም፣

55 በልብስና በቤት ላይ ለሚመጣ ተላላፊ በሽታ፣

56 ለዕብጠት፣ ለችፍታ ወይም ለቋቊቻ፣

57 አንድ ነገር ንጹሕ ወይም ርኩስ መሆኑ የሚታወቅበት ነው። ይህ ተላላፊ የቈዳ በሽታ እንዲሁም በልብስና በቤት ላይ ለሚወጣ ተላላፊ በሽታ የሚያገለግል ሕግ ነው።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27