ዘሌዋውያን
ምዕራፎች 6
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
2“ማንኛውም ሰው በዐደራ የተሰጠውን ወይም በመያዣነት የተቀበለውን በመካድና ባልንጀራውን በማጭበርበር ኀጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔርንም (ያህዌ) ቢበድል ወይም ባልንጀራውን ቢቀማው ወይም ቢያታልለው፣
3ወይም የጠፋ ነገር አግኝቶ አላየሁም ቢል ወይም በሐሰት ቢምል ወይም ሰዎች የሚያደርጉትን እንዲህ ያለውን ማናቸውንም ኀጢአት ቢሠራ፣
4በዚህ ሁኔታ ኀጢአት ቢሠራና በደለኛ ቢሆን፣ የሰረቀውን ወይም የቀማውን ወይም በዐደራ የተሰጠውን ወይም ጠፍቶ ያገኘውን ይመልሳል፤
5በሐሰት የማለበትንም ሁሉ ይመልስ፤ የበደል መሥዋዕቱን በሚያቀርብበት ጊዜ የወሰደውን በሙሉ የዋናውን አንድ አምስተኛ በመጨመር ለባለ ንብረቱ ይመልስ።
6ከመንጋውም እንከን የሌለበትን ዋጋው ተመጣጣኝ የሆነ አውራ በግ ስለ በደሉ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ለማቅረብ ወደ ካህኑ ያምጣ፤
7በዚህም ሁኔታ ካህኑ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ስለ ፈጸመው ስለማንኛውም በደል ይቅር ይባላል።