ዘሌዋውያን
ምዕራፎች 22
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
2“እስራኤላውያን ቀድሰው ለእኔ የለዩትን ቅዱስ መሥዋዕት በአክብሮት ባለመያዝ፣ ቅዱስ ስሜን እንዳያረክሱ ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
3“እንዲህም በላቸው፤ ‘በሚቀጥሉት ትውልዶች ከዘርህ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ ያልሆነ ማንኛውም ሰው፣ እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ለይተው ወዳቀረቡት ቅዱስ መሥዋዕት ቢቀርብ ያ ሰው ከፊቴ ይወገድ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
4“ ‘ከአሮን ዘር ተላላፊ የቈዳ በሽታ ያለበት ወይም ከሰውነቱ ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ማንኛውም ሰው እስኪነጻ ድረስ ቅዱሱን መሥዋዕት አይብላ፤ እንዲሁም በአስከሬን የረከሰውን ነገር ወይም የዘር ፈሳሽ ያለበትን ሰው ቢነካ፣
5ወይም በደረቱ የሚሳብ የሚያረክስ ነገርን ወይም የሚያረክስ ማንኛውንም ሰው ቢነካ፣ የቱንም ዐይነት ርኵሰት ቢሆን፣
6እንዲህ ያለውን ማንኛውንም ነገር የሚነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ሰውነቱንም በውሃ ካልታጠበ፣ ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን መሥዋዕት አይብላ።
7ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ ንጹሕ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ የተቀደሰውን መሥዋዕት መብላት ይችላል፤ ምግቡ ነውና።
8እንዳይረክስ ማንኛውንም ሞቶ የተገኘውን ወይም አውሬ የዘነጠለውን አይብላ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
9“ ‘ካህናት ትእዛዛቴን በመናቅ በደለኛ እንዳይሆኑና እንዳይሞቱ ይጠብቋቸው፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
10“ ‘ከካህን ቤተ ሰብ በቀር የካህኑ እንግዳም ሆነ ቅጥር ሠራተኛ የተቀደሰውን መሥዋዕት አይብላ።
11ነገር ግን ካህኑ በገንዘብ የገዛው ወይም በቤቱ የተወለደ ባሪያ ቢኖረው፣ ያ ባሪያ ከካህኑ ድርሻ መብላት ይችላል።
12የካህን ልጅ፣ ካህን ያልሆነ ሌላ ሰው ካገባች፣ ከተቀደሰው መሥዋዕት መብላት አትችልም።
13ይሁን እንጂ የካህኑ ልጅ ባሏ ቢሞት ወይም ብትፋታ፣ ልጆችም ባይኖሩዋትና እንደ ልጅነት ጊዜዋ በአባቷ ቤት ለመኖር ብትመለስ፣ ከአባቷ ድርሻ መብላት ትችላለች፤ ያልተፈቀደለት ሰው ግን ከተቀደሰው መሥዋዕት መብላት አይችልም።
14“ ‘ማንኛውም ሰው ባለማወቅ የተቀደሰውን መሥዋዕት ቢበላ፣ የመሥዋዕቱን አንድ አምስተኛ ጨምሮ ለካህኑ ይተካ።
15እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያቀርቡትን የተቀደሰ መሥዋዕት ካህናቱ አያርክሱት፤
16ይህንኑ የተቀደሰ መሥዋዕት እንዲበሉና ቅጣት የሚያስከትል በደል እንዲፈጽሙ አያድርጉ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።