1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
2 “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ሴት አርግዛ ወንድ ልጅ በምትወልድበት ጊዜ፣ ልክ እንደ ወር አበባዋ ጊዜ እስከ ሰባት ቀን ትረክሳለች።
3 ሕፃኑም በስምንተኛው ቀን ይገረዝ።
4 ሴትዮዋም ከደሟ እስክትነጻ ድረስ ሠላሳ ሦስት ቀን ትቆይ፤ የመንጻቷም ወራት እስኪፈጸም ድረስ ማንኛውንም የተቀደሰ ነገር አትንካ፤ ወደ ቤተ መቅደስም አትግባ።
5 ነገር ግን የወለደችው ሴት ልጅ ከሆነ፣ እንደ ወር አበባዋ ጊዜ ሁለት ሳምንት ትረክሳለች፤ ከዚያም ከደሟ እስክትነጻ ስድሳ ስድስት ቀን ትቆይ።
6 “ ‘ሴትዮዋ ወንድ ወይም ሴት ልጅዋን ወልዳ የመንጻትዋ ጊዜ ሲፈጸም፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት የአንድ ዓመት ጠቦት፣ ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ የዋኖስ ጫጩት ወይም አንድ ርግብ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወስዳ ካህኑ ዘንድ ታቅርብ።
7 ካህኑም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርበው፤ ያስተሰርይላትም፤ ሴትዮዋም ከደሟ ፈሳሽ ትነጻለች።“ ‘ሴትዮዋ ወንድ ወይም ሴት ብትወልድ ሕጉ ይኸው ነው።
8 ጠቦት ለማምጣት ዐቅምዋ ካልፈቀደ፣ ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች፣ አንዱ ለሚቃጠል መሥዋዕት፣ ሌላው ደግሞ ለኀጢአት መሥዋዕት ታቅርብ፤ በዚህም ካህኑ ያስተሰር ይላታል፤ እርሷም ትነጻለች።’ ”