ዘሌዋውያን 8 NASV

አሮንና ልጆቹ ካህናት ሆነው መሾማቸው

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

2 “አሮንንና ልጆቹን፣ ልብሰ ተክህኖውን፣ የመቅቢያ ዘይቱን፣ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን፣ ሁለቱን አውራ በጎችና እርሾ ሳይገባበት የተጋገረው ቂጣ ያለበትን መሶብ አምጣ፤

3 ማኅበሩን በሙሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሰብስብ።”

4 ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው አደረገ፤ ማኅበሩም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተሰበሰበ።

5 ሙሴም ማኅበሩን፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲደረግ ያዘዘው ይህ ነው” አላቸው።

6 ሙሴም አሮንንና ልጆቹን ወደ ፊት አወጣቸው፤ በውሃም አጠባቸው።

7 አሮንን እጀ ጠባብ አለበሰው፤ መቀነት አስታጠቀው፤ ቀሚስ አጠለቀለት፤ ኤፉድ ደረበለት፤ በልዩ ጥበብ በተጠለፈው መታጠቂያ ኤፉዱን አስታጠቀው፤ በላዩም አሰረው፤

8 የደረት ኪሱን በላዩ አደረገለት፤ በደረት ኪሱም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን አኖረ።

9 እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘውም መሠረት፣ ሙሴ ጥምጥሙን በአሮን ራስ ላይ አደረገ፤ በጥምጥሙም ላይ በፊት ለፊቱ በኩል የተቀደሰውን አክሊል አደረገለት።

10 ሙሴም መቅቢያ ዘይቱን ወሰደ፤ ማደሪያ ድንኳኑንና በውስጡ የሚገኘውን ሁሉ ቀብቶ ቀደሰ።

11 ከዘይቱም ጥቂት ወስዶ በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ ይቀድ ሳቸውም ዘንድ መሠዊያውን ከነመገልገያ ዕቃው ሁሉ እንዲሁም የመታጠቢያ ሳሕኑን ከነማስቀመጫው በዘይት ቀባ።

12 ከመቅቢያ ዘይቱም በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፤ የተቀደሰ እንዲሆንም ቀባው።

13 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት ሙሴ፣ የአሮንን ልጆች ወደ ፊት አቅርቦ እጀ ጠባብ አለበሳቸው፤ መታጠቂያ አስታጠቃቸው፤ ቆብም ደፋላቸው።

14 ሙሴም የኀጢአት መሥዋዕት የሆነውን ወይፈን አመጣ፤ አሮንና ልጆቹም በወይፈኑ ራስ ላይ እጃቸውን ጫኑ።

15 ሙሴም ወይፈኑን ዐረደ፤ ደሙንም ወስዶ መሠዊያውን ያነጻ ዘንድ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ሁሉ ቀባ፤ የቀረውንም ደም በመሠዊያው ሥር አፈሰሰው። ለመሠዊያውም እንዲህ አድርጎ ያስተሰርይለት ዘንድ ቀደሰው።

16 ሙሴም የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሁሉ፣ የጒበቱን ሽፋን፣ ኵላሊቶችንና ሥባቸውን ወስዶ በመሠዊያው ላይ አቃጠለ።

17 ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት ወይፈኑን፣ ቈዳውን፣ ሥጋውንና ፈርሱን ከሰፈር ውጭ አቃጠለ።

18 ሙሴ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም እጃቸውን በበጉ ላይ ጫኑ።

19 ሙሴም በጉን ዐርዶ ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ።

20 በጉንም በየብልቱ ቈራረጠ፤ ጭንቅላቱን፣ ብልቶቹንና ሥቡን አቃጠለ።

21 ሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ አጠበ፤ ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት፣ በጉን በሙሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው።

22 ሙሴ ለቅድስና የሚሆነውን ሌላ አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በበጉ ራስ ላይ ጫኑ።

23 ሙሴ አውራ በጉን ዐረደ፤ ከደሙም ጥቂት ወስዶ የአሮንን ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት አስነካ፤

24 የአሮንንም ልጆች ወደ ፊት ጠራ፤ ከደሙም ጥቂት ወስዶ የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፣ የቀኝ እጃቸውን አውራ ጣትና የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት አስነካ፤ የቀረውንም ደም በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ።

25 ሥቡን፣ ላቱን፣ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ ሁሉ፣ የጒበቱን ሽፋን፣ ሁለቱን ኵላሊቶችና ሥባቸውን እንዲሁም ቀኝ ወርቹን ወሰደ፤

26 በእግዚአብሔርም (ያህዌ) ፊት ካለው፣ ያለ እርሾ የተጋገረ ዳቦ ካለበት መሶብ ላይ አንድ ኅብስት፣ አንድ በዘይት የተጋገረ ዳቦ እንዲሁም ስስ ቂጣ ወስዶ በሥቦቹና በቀኝ ወርቹ ላይ አኖረ።

27 እነዚህንም ሁሉ ለአሮንና ለልጆቹ በእጃቸው ሰጣቸው፤ እነርሱም የሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወዘወዙት።

28 ሙሴም ከእጃቸው ተቀብሎ፣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አቃጠለው።

29 ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት፣ ድርሻው የሆነውን ክህነት የመስጫውን አውራ በግ ፍርምባ ወስዶ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወዘወዘው።

30 ቀጥሎም ሙሴ በመቅቢያው ዘይትና በመሠዊያው ላይ ካለው ደም ጥቂት ወስዶ፣ በአሮንና በልብሱ እንዲሁም በአሮን ልጆችና በልብሳቸው ላይ ረጨ፤ በዚህም ሁኔታ አሮንንና ልብሱን፣ ልጆቹንና ልብሳቸውን ቀደሰ።

31 ሙሴም አሮንና ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “ሥጋውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቀቅሉት፤ በዚያም፣ ‘አሮንና ልጆቹ ይብሉት’ ተብዬ በታዘዝሁት መሠረት፣ በክህነት መስጫው መሥዋዕት መሶብ ውስጥ ካለው ኅብስት ጋር ብሉት፤

32 የተረፈውንም ሥጋና ኅብስት በእሳት አቃጥሉ።

33 የክህነት መቀበያችሁ ሥርዐት እስከሚፈጸምበት እስከ ሰባት ቀን ድረስ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቆዩ፤ ሥርዐቱንም ለመፈጸም ሰባት ቀን ይወስዳልና።

34 ዛሬ የተፈጸመው ይህ ሥርዐት ለእናንተ ማስተሰረያ እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ነው።

35 እንዳትሞቱ ሰባቱን ቀንና ሌሊት ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትለዩ፤ የእግዚአብሔርንም (ያህዌ) ሥርዐት ጠብቁ፤ የታዘዝሁት እንዲህ ነውና።”

36 አሮንና ልጆቹም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27