ዘሌዋውያን 19 NASV

ልዩ ልዩ ሕግጋት

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

2 “ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ጉባኤ እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ።

3 “ ‘ከእናንተ እያንዳንዱ እናቱንና አባቱን ያክብር፤ ሰንበታቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

4 “ ‘ወደ ጣዖታት ዘወር አትበሉ፤ ወይም ከቀለጠ ብረት ለራሳችሁ አማልክት አትሥሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

5 “ ‘የኅብረት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በምታቀርቡበት ጊዜ፣ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲያገኝላችሁ አድርጋችሁ አቅርቡ።

6 መሥዋዕቱም ባቀረባችሁት ዕለት ወይም በማግሥቱ ይበላ፤ እስከ ሦስተኛው ቀን የተረፈ ማንኛውም ነገር ይቃጠል።

7 በሦስተኛውም ቀን ቢበላ ርኩስ ነው፤ ተቀባይነትም የለውም።

8 ከመሥዋዕቱ የሚበላ ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰውን ነገር አርክሶአልና ይጠየቅበታል፤ ያም ሰው ከወገኑ ተለይቶ ይጥፋ።

9 “ ‘የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ፣ በእርሻችሁ ዳርና ዳር ያለውን አትጨዱ፤ ቃርሚያውንም አትልቀሙ።

10 የወይንህን እርሻ አትቃርም፤ የወደቀውንም አትልቀም፤ ለድኾችና ለመጻተኞች ተውላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

11 “ ‘አትስረቁ፤“ ‘አትዋሹ፤“ ‘ከእናንተ አንዱ ሌላውን አያታል።

12 “ ‘በስሜ በሐሰት አትማሉ፤ በዚህም የአምላካችሁን (ኤሎሂም) ስም አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

13 “ ‘ባልንጀራህን አታጭበርብር፤ አትቀማውም፤“ ‘የሙያተኛውን ደመወዝ ሳትከፍል አታሳድር።

14 “ ‘ደንቈሮውን አትርገም፤ በዐይነ ስውሩም ፊት ዕንቅፋት አታኑር፤ ነገር ግን አምላክህን (ኤሎሂም) ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

15 “ ‘ፍርድ አታዛቡ፤ ለድኻው አታድላለት፤ ለትልቁም ሰው ልዩ አክብሮት አትስጥ፤ ለብርቱው አታዳላ፤ ነገር ግን ለባልንጀራህ በትክክል ፍረድ።

16 “ ‘በሕዝብህ መካከል ሐሜት አትንዛ፤“ ‘የባልንጀራህን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ነገር አታድርግ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

17 “ ‘ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ የበደሉ ተካፋይ እንዳትሆን ባልንጀራህን በግልጽ ገሥጸው።

18 “ ‘ወገንህን አትበቀል፤ ወይም ምቀኛ አትሁንበት፤ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

19 “ ‘ሥርዐቴን ጠብቁ፤“ ‘የተለያዩ እንስሳትን አታዳቅል፤“ ‘በዕርሻህ ላይ ሁለት ዐይነት ዘር አትዝራ፤“ ‘ከሁለት ዐይነት ነገር የተሠራ ልብስ አትልበስ።

20 “ ‘አንድ ሰው ለሌላ ከታጨች ሴት ባሪያ ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ሴቲቱም ያልተዋጀች ወይም ነጻ ያልወጣች ብትሆን ይቀጣል፤ ነገር ግን ሴቲቱ ነጻ ስላልወጣች አይገደሉም።

21 ሰውየውም ለበደል መሥዋዕት የሚሆን አንድ አውራ በግ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያምጣ።

22 ካህኑም በበደል መሥዋዕቱ አውራ በግ፣ ሰውየው ስለ ሠራው ኀጢአት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይቅር ይባልለታል።

23 “ ‘ወደ ምድሪቱ ገብታችሁ ማንኛውንም ዐይነት ፍሬ የሚሰጥ ዛፍ በምትተክሉበት ጊዜ፣ ፍሬው ለመብላት የተከለከለ መሆኑን ዕወቁ፤ ለሦስት ዓመትም የተከለከለ በመሆኑ አይበላ።

24 በአራተኛውም ዓመት ፍሬው ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰ የምስጋና መሥዋዕት ይሆናል።

25 በአምስተኛው ዓመት ግን ፍሬውን ትበላላችሁ፤ በዚህም ሁኔታ ፍሬው ይበዛላችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

26 “ ‘ደም ያለበትን ማንኛውንም ሥጋ አትብሉ፤“ ‘ጥንቈላ ወይም አስማት አትሥሩ።

27 “ ‘የራስ ጠጒራችሁን ዙሪያ አትከርከሙ፤ ጢማችሁንም አሳጥራችሁ አትቊረጡ።

28 “ለሞተ ሰው ሰውነታችሁን አትንጩ፤ በሰውነታችሁም ላይ ንቅሳት አታድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

29 “ ‘ምድሪቱ ወደ ግልሙትና አዘንብላ በርኵሰት እንዳትሞላ፣ ሴት ልጅህ ጋለሞታ ትሆን ዘንድ አታዋርዳት።

30 “ ‘ሰንበታቴን ጠብቁ፤ መቅደሴንም አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

31 “ ‘እንዳትረክሱባቸው ወደ ሙታን ጠሪዎች ዘወር አትበሉ፤ መናፍስት ጠሪዎችንም አትፈልጉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

32 “ዕድሜው ለገፋ ተነሥለት፤ ሽማግሌውን አክብር፤ አምላክህንም (ኤሎሂም) ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

33 “ ‘መጻተኛ በምድራችሁ ላይ አብሮአችሁ በሚኖርበት ጊዜ አትበድሉት፤

34 አብሮአችሁ የሚኖረው መጻተኛ እንደገዛ ወገናችሁ ይታይ፤ እንደ ራሳችሁም ውደዱት፤ እናንተም በግብፅ መጻተኞች ነበራችሁና፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

35 “ ‘በመስፈሪያ ወይም በሚዛን አታጭ በርብሩ።

36 እውነተኛ መለኪያ፣ እውነተኛ መመዘኛ፣ እውነተኛ የኢፍ መስፈሪያ፣ እውነተኛ የኢን መስፈሪያ ይኑራችሁ። ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

37 “ ‘ሥርዐቴንና ሕጌን ሁሉ ጠብቁ፤ ተከተሏቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።’ ”

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27