ዘሌዋውያን 20 NASV

ኀጢአት የሚያስከትለው ቅጣት

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

2 “ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘ከልጆቹ አንዱን ለሞሎክ የሚሰጥ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር መጻተኛ ይገደል፤ እርሱንም የአገሩ ሕዝብ በድንጋይ ይውገረው።

3 ልጁን ለሞሎክ በመስጠት መቅደሴን አርክሶአልና፣ ቅዱሱን ስሜንም አቃልሎአልና፣ በዚያ ሰው ላይ ጠላት እሆንበታለሁ፤ ከወገኖቹም ለይቼ አጠፋዋለሁ።

4 የአገሩ ሕዝብ፣ ሰውየው ልጁን ለሞሎክ ሲሰጥ አይተው ቸል ቢሉ፣ ባይገድሉትም፣

5 በዚያ ሰውና በቤተ ሰቡ ላይ ጠላት እሆናለሁ፤ እርሱንና ከሞሎክ ጋር በማመንዘር እርሱን የተከተሉትን ሁሉ ከሕዝባቸው መካከል ለይቼ አጠፋቸዋለሁ።

6 “ ‘ወደ ሙታን ጠሪዎችና ጠንቋዮች ዘወር በማለት፣ በሚከተላቸውና ከእነርሱም ጋር በሚያመነዝር ሰው ላይ ጠላት እሆንበታለሁ፤ ከወገኖቹም ለይቼ አጠፋዋለሁ።

7 “ ‘ራሳችሁን ቀድሱ፤ ቅዱሳንም ሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝና።

8 ሥርዐቴን ጠብቁ፤ አድርጉትም፤ የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።

9 “ ‘አባቱን ወይም እናቱን የሚረግም ማንኛውም ሰው ይገደል፤ አባቱን ወይም እናቱን ረግሞአልና፤ ደሙ በራሱ ላይ ነው።

10 “ ‘አንድ ሰው ከባልንጀራው ሚስት ጋር ቢያመነዝር፣ አመንዝራውና አመንዝራዪቱ ይገደሉ።

11 “ ‘አንድ ሰው ከአባቱ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም አባቱን አዋርዶአል፤ ሰውየውና ሴትዮዋ ይገደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።

12 “ ‘አንድ ሰው ከልጁ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ሁለቱም ይገደሉ፤ ነውር አድርገዋልና ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።

13 “ ‘አንድ ወንድ ከሴት ጋር ግብረ ሥጋ እንደሚፈጽም ሁሉ ከወንድ ጋር ቢፈጽም፣ ሁለቱም አስጸያፊ ድርጊት ፈጽመዋልና ይገደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።

14 “ ‘አንድ ሰው አንዲትን ሴትና እናትዋን ቢያገባ፣ አድራጐቱ ጸያፍ ነው፤ በመካከላችሁ እንዲህ ዐይነት ርኵሰት እንዳይገኝ ሰውየውና ሴቶቹ በእሳት ይቃጠሉ።

15 “ ‘ማንኛውም ሰው ከእንስሳ ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ይገደል፤ እንስሳዪቱንም ግደሏት።

16 “ ‘አንዲት ሴት ወደ እንስሳ ቀርባ ግብረ ሥጋ ብትፈጽም፣ ሴቲቱንና እንስሳውን ግደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።

17 “ ‘አንድ ሰው የአባቱ ወይም የእናቱ ልጅ የሆነችውን እኅቱን አግብቶ ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ አድራጎቱ አሳፋሪ ነው፤ በሕዝባቸው ፊት ከሕዝባቸው ተለይተው ይጥፉ። ሰውየው እኅቱን አዋርዶአልና ይጠየቅበታል።

18 “ ‘ማንኛውም ሰው በወር አበባዋ ጊዜ ከሴት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ የፈሳሿን ምንጭ ገልጦአልና፣ እርሷም የፈሳሿን ምንጭ ገልጣለችና፣ ሁለቱም ከሕዝባቸው መካከል ተለይተው ይጥፉ።

19 “ ‘ከእናትህም ሆነ ከአባትህ እኅት ጋር ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ይህ የሥጋ ዝምድናን ማቃለል ስለ ሆነ ሁለታችሁም ትጠየቁበታላችሁ።

20 “ ‘ማንኛውም ሰው ከአጎቱ ሚስት ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ አጎቱን አዋርዶአልና ሁለቱም ይጠየቁበታል፤ ያለ ልጅም ይሞታሉ።

21 “ ‘ማንኛውም ሰው የወንድሙን ሚስት ቢያገባ አድራጐቱ ርኵሰት ነው፤ ወንድሙን አዋርዶአልና፣ ያለ ልጅም ይቀራሉ።

22 “ ‘እንድትኖሩባት እናንተን የማስገባባት ምድር እንዳትተፋችሁ ሥርዐቴንና ሕጌን ጠብቁ፤ አድርጉም።

23 ከፊታችሁ የማሳድዳቸውን አሕዛብ ልማድ አትከተሉ፤ እነዚህን ሁሉ በማድረጋቸው ተጸየፍኋቸው።

24 እናንተ ግን፣ “ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ ማርና ወተት የምታፈሰውን አገር ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ” አልኋችሁ፤ ከአሕዛብ የለየኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።

25 “ ‘ንጹሕ በሆኑትና ንጹሕ ባልሆኑት እንስሳት እንዲሁም ንጹሕ በሆኑትና ንጹሕ ባልሆኑት ወፎች መካከል ልዩነት አድርጉ። ርኩስ ነው ብዬ በለየሁት በማንኛውም እንስሳ ወይም ወፍ ወይም በምድር ላይ በሚንቀሳቀስ በማንኛውም ነገር ራሳችሁን አታርክሱ።

26 እናንተ ለእኔ ቅዱሳን ትሆኑልኛላችሁ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ቅዱስ ነኝና፤ የኔ ትሆኑ ዘንድ ከአሕዛብ መካከል ለይቻችኋለሁ።

27 “ ‘ከመካከላችሁ ሙታን ጠሪ ወይም መናፍስት ጠሪ የሆነ ማንኛውም ወንድ ወይም ሴት ይገደል፤ በድንጋይም ይወገሩ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።’ ”

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27