1 “ ‘እጅግ ቅዱስ የሆነው የበደል መሥዋዕት የአቀራረብ ሥርዐት ይህ ነው፦
2 የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የበደሉም መሥዋዕት እዚያው ይታረድ፤ ደሙም በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ይረጭ።
3 ሥቡን በሙሉ ያቅርብ፤ ይኸውም፦ ላቱን፣ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ፣
4 ሁለቱ ኵላሊቶች፣ በኵላሊቶቹ ላይና በጐድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ እንዲሁም ከኵላሊቶቹ ጋር የሚወጣውን የጒበቱን ሽፋን አብሮ ያቅርብ።
5 ካህኑም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ይህም የበደል መሥዋዕት ነው።
6 ከካህን ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ከዚህ መብላት ይችላል፤ ነገር ግን በተቀደሰ ስፍራ ይበላ፤ ይህም እጅግ ቅዱስ ነው።