24 ስለዚህ፣ ‘ማንኛውም ዐይነት የወርቅ ጌጣጌጥ ያለው ሁሉ ያውልቀው አልኋቸው፤ ከዚያም ወርቁን ሰጡኝ፤ ወደ እሳቱ ጣልሁት፤ ይህም ጥጃ ወጣ።”
25 ሕዝቡ ከቍጥጥር ውጭ እንደሆኑ፣ አሮንም መረን እንደ ለቀቃቸውና በጠላቶቻቸውም ዘንድ መሳለቂያ እንደሆኑ ሙሴ አስተዋለ።
26 ስለዚህ በሰፈሩ መግቢያ ላይ ቆሞ፣ “የእግዚአብሔር (ያህዌ) የሆነ ሁሉ ወደ እኔ ይምጣ” አለ፤ ሌዋውያኑም ሁሉ ከእርሱ ጋር ሆኑ።
27 ከዚያም፣ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ ሰው በወገቡ ላይ ሰይፍ ይታጠቅ፤ በሰፈር ውስጥ ከዳር እዳር እየተመላለሰ እያንዳንዱ ወንድሙን፣ ጓደኛውንና ጎረቤቱን ይግደል’ ” አላቸው።
28 ሌዋውያኑ ሙሴ እንዳዘዛቸው ፈጸሙ፤ በዚያኑም ዕለት ከሕዝቡ ሦስት ሺህ ያህል አለቁ።
29 ከዚያም ሙሴ፣ “በራሳችሁ ወንዶች ልጆችና ወንድሞች ላይ በመነሣታችሁ፣ በዛሬዋ ቀን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተለያችሁ ሆናችኋል፤ በዛሬዋም ዕለት ባርኳችኋል” አለ።
30 በማግሥቱም ሙሴ ሕዝቡን፣ “እጅግ የከፋ ኀጢአት ሠርታችኋል፤ አሁን ግን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) እወጣለሁ፤ ምናልባት ኀጢአታችሁን ማስተስረይ እችል ይሆናል” አላቸው።