1 ከጥቂት ጊዜ በኋላ በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ የወይን ተክል ቦታ ላይ አንድ ነገር ደረሰ፤ ቦታውም በኢይዝራኤል ውስጥ ከሰማርያ ንጉሥ ከአክዓብ ቤተ መንግሥት አጠገብ ነበር።
2 አክዓብም ናቡቴን፣ “የወይን ተክል ቦታህ ከቤተ መንግሥቴ አጠገብ ስለ ሆነ፣ የአትክልት ቦታ እንዳደርገው ልቀቅልኝ፤ በምትኩ ከዚህ የበለጠ የወይን ተክል ቦታ እሰጥሃለሁ፤ የተሻለ ሆኖ ከታየህም የሚያወጣውን ገንዘብ እከፍልሃለሁ” አለው።
3 ናቡቴ ግን፣ “ዐፅመ ርስቴን እለቅልህ ዘንድ እግዚአብሔር አይበለው” ሲል መለሰለት።
4 ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ፣ “ዐፅመ ርስቴን አልለቅልህም” ስላለው፣ አክዓብ ተበሳጭቶና ተቈጥቶ ወደ ቤቱ ገባ፤ አኵርፎም በዐልጋው ላይ ተኛ፤ ምግብም መብላት ተወ።
5 ሚስቱ ኤልዛቤልም ወደ እርሱ ገብታ፣ “እስከዚህ የተበሳጨኸው፣ ምግብስ የማትበላው ለምንድን ነው?” ብላ ጠየቀችው።
6 እርሱም፣ “ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን፣ ‘የወይን ተክል ቦታህን ሽጥልኝ፤ ከፈለግህም በምትኩ ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ’ አልሁት፤ እርሱ ግን፣ ‘የወይን ተክል ቦታዬን አልለቅልህም’ ስላለኝ ነው” አላት።