28 የዕቃ ማስቀመጫዎቹ የተሠሩት እንደዚህ ነው፤ እነዚህም ቀጥ ብለው ከቆሙ ደጋፊዎች ጋር የተያያዙ ባለ አራት ማእዘን ጠፍጣፋ ናሶች ነበሯቸው።
29 ዳርና ዳር ባሉት ድጋፎች መካከል በሚገኙት ጠፍጣፋ ናሶች ላይ የአንበሶችን፣ የኮርማዎችንና የኪሩቤልን ምስል አደረገ፤ በድጋፎቹም ላይ እንደዚሁ አደረገ። ከአንበሶቹና ከኮርማዎቹ በላይና በታች በኩል ደግሞ የአበባ ጒንጒን የሚመስሉ ተቀጥቅጠው የተሠሩ ቅርጾች ነበሩ።
30 እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት የናስ መንኰራኵርና መንኰራኵሮቹ የሚሽከረከሩባቸው የናስ ወስከምቶች እንዲሁም እያንዳንዳቸው በአራቱም ማእዘን ገጽ ላይ የአበባ ጒንጒን ቀልጦ የተሠራባቸው የመታጠቢያ ገንዳ መደገፊያዎች ነበረው።
31 በዕቃ ማስቀመጫወቹም ውስጥ ጥልቀቱ አንድ ክንድ የሆነ ባለ ክብ ክፍተት ነበር፤ ይህም ክፍተት ድቡልቡል ሆኖ ከታች ከመቆሚያው በኩል ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ወርድ ሲኖረው፣ በክፍተቱም ዙሪያ ቅርጾች ነበሩ፤ ክፈፎቹ ግን ባለ አራት ማእዘን እንጂ ክብ አልነበሩም።
32 አራቱ መንኰራኵሮች በዕቃ ማስቀመጫው ጠፍጣፋ ናስ ሥር ሲሆኑ፣ የመንኰራኵሮቹ ወስከምቶች ደግሞ ከዕቃ ማስቀመጫዎቹ ጋር የተያያዙ ነበሩ፤ የእያንዳንዱም መንኰራኵር ስፋት አንድ ክንድ ተኩል ነበር።
33 መንኰራኵሮቹ የሠረገላ መንኰራኵር መሰል ሲሆኑ፣ ወስከምቶቹ የመንኮራኵሮቹ ክፈፎችና ዐቃፊዎቻቸው እንዲሁም ወስከምቶቹ የሚገቡባቸው ቧምቧዎች በሙሉ ከቀለጠ ብረት የተሠሩ ነበሩ።
34 እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት ወጣ ያለ እጀታ ነበረው።