7 ዮሐንስም በእርሱ እጅ ሊጠመቁ የወጡትን ሰዎች እንዲህ ይላቸው ነበር፤ “እናንት የእፉኝት ልጆች፣ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን መከራችሁ?
8 እንግዲህ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አፍሩ፤ ደግሞም በልባችሁ፣ ‘አብርሃም አባታችን አለን’ ማለትን አትጀምሩ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ማስነሣት እንደሚችል እነግራችኋለሁና።
9 አሁን እንኳ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራም ዛፍ ሁሉ ተቈርጦ ወደ እሳት ይጣላል።”
10 ሕዝቡም፣ “ታዲያ፣ ምን እናድርግ?” ብለው ጠየቁት።
11 ዮሐንስም፣ “ሁለት ልብስ ያለው ምንም ለሌለው ያካፍል፤ ምግብ ያለውም እንዲሁ ያድርግ” ብሎ መለሰላቸው።
12 ቀረጥ ሰብሳቢዎችም ሊጠመቁ ወደ እርሱ መጥተው፣ “መምህር ሆይ፤ እኛስ ምን እናድርግ?” አሉት።
13 እርሱም፣ “ከታዘዛችሁት በላይ ቀረጥ አትሰብስቡ” አላቸው።