1 ነገሥት 10:20-26 NASV

20 በስድስቱም ደረጃ ጫፍ ላይ ግራና ቀኝ ስድስት ስድስት አንበሶች ቆመዋል። ይህን የመሰለም ዙፋን በየትኛውም አገር መንግሥት ከቶ ተሠርቶ አያውቅም።

21 ንጉሥ ሰሎሞን የሚጠጣበት ዋንጫ ሁሉ የወርቅ ሲሆን፣ የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበረው ዕቃ በሙሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠራ ነበር፤ በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ብር ይህን ያህል ዋጋ ስላልነበረው፣ ከብር የተሠራ ዕቃ ፈጽሞ አልነበረም።

22 ንጉሡ ከኪራም መርከቦች ጋር አብረው በባሕር ላይ የሚጓዙ የተርሴስ የንግድ መርከቦች ነበሩት። እነዚህም በየሦስት ዓመቱ አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብርና የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣዎችና ዝንጀሮዎች ያመጡ ነበር።

23 ንጉሥ ሰሎሞንም በሀብትና በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ ነበር።

24 ዓለሙ ሁሉ እግዚአብሔር በሰሎሞን ልብ ያኖረውን ጥበብ ለመስማት ወደ እርሱ መምጣት ይፈልግ ነበር።

25 በየዓመቱም የሚመጣውን ሰው ሁሉ የብርና የወርቅ ዕቃ፣ ልብስ፣ የጦር መሣሪያ፣ ሽቶ፣ ፈረስና በቅሎ ስጦታ አድርጎ ያመጣለት ነበር።

26 ሰሎሞን ሠረገሎችና ፈረሶች ሰበሰበ፤ አንድ ሺህ አራት መቶ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሶች ነበሩት። እነዚህንም ሁሉ ሠረገሎች በሚያኖርበት ከተሞችና ራሱ በሚኖርበት በኢየሩሳሌም እንዲሆኑ አደረገ።