5 እንዲሁም በገበታው ላይ የሚቀርበውን መብል፣ የሹማምቱን አቀማመጥ፣ አሳላፊዎቹን ከነደንብ ልብሳቸው፣ ጠጅ አሳላፊዎቹን፣ ደግሞም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያቀረበውን የሚቃጠል መሥዋዕት ስታይ እጅግ ተደነቀች።
6 ንጉሡንም እንዲህ አለችው፤ “ስላከናወንኸው ሥራና ስለ ጥበብህ ባገሬ ሳለሁ የሰማሁት ትክክል ነው፤
7 ይሁን እንጂ፣ ራሴ መጥቼ እነዚህን ነገሮች በዐይኔ እስካይ ድረስ አላመንሁም ነበር፤ በእርግጥ ግማሹን እንኳ አልነገሩኝም፤ ጥበብህና ብልጽግናህ ከሰማሁት በላይ ነው።
8 ሰዎችህ እንዴት ያሉ ዕድለኞች ናቸው! ሁል ጊዜ በፊትህ ቆመው ጥበብህን የሚሰሙ ሹማምትህስ እንዴት የታደሉ ናቸው!
9 በአንተ ደስ ተሰኝቶ በእስራኤል ዙፋን ላይ ያስቀመጠህ እግዚአብሔር አምላክህ የተመሰገነ ይሁን፤ እግዚአብሔር በዘላለም ፍቅሩም እስራኤልን ከመውደዱ የተነሣ፣ ፍትሕና ጽድቅ እንዲሰፍን አንተን ንጉሥ አድርጎ አስነሣህ።”
10 ለንጉሡም መቶ ሃያ መክሊት ወርቅ፣ እጅግ ብዙ ሽቶና የከበረ ድንጋይ ሰጠችው፤ ንግሥተ ሳባ ለንጉሥ ሰሎሞን ያበረከተችለትን ያን ያህል ብዛት ያለው ሽቶ ከዚያ በኋላ ከቶ አልመጣም።
11 ከኦፊር ወርቅ ያመጡት የኪራም መርከቦች፣ እጅግ ብዙ የሰንደል ዕንጨትና የከበሩ ዕንቆችም አመጡ።