1 ነገሥት 11:2-8 NASV

2 እነዚህም እግዚአብሔር እስራኤላውያንን፣ “ልባችሁን ወደ አማልክታቸው በርግጥ ይመልሱታልና ከእነርሱ ጋር መጋባት የለባችሁም” ካላቸው አሕዛብ ወገን ነበሩ፤ ሆኖም ሰሎሞን ከእነዚሁ ጋር ፍቅሩ ጠና።

3 እርሱም ከነገሥታት የተወለዱ ሰባት መቶ ሚስቶችና ሦስት መቶ ቁባቶች ነበሩት፤ ሚስቶቹም ልቡ ወደ ሌላ እንዲያዘነብል አደረጉት።

4 ሰሎሞን በሸመገለ ጊዜ ሚስቶቹ ልቡን ወደ ሌሎች አማልክት መለሱት፤ የአባቱ የዳዊት ልብ እንደ ተገዛ ሁሉ፣ በፍጹም ልቡ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር አልተገዛም።

5 ሰሎሞንም የሲዶናውያንን ሴት አምላክ አስታሮትን፣ አስጸያፊውን የአሞናውያንን አምላክ ሚልኮምን ተከተለ።

6 ስለዚህ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ እንደ አባቱ እንደ ዳዊትም እግዚአብሔርን እስከ መጨረሻው አልተከተለም።

7 ሰሎሞን ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ባለው ተራራ ላይ ለአስጸያፊው የሞዓብ አምላክ ለካሞሽ እንዲሁም አስጸያፊ ለሆነው ለአሞናውያን አምላክ ለሞሎክ ማምለኪያ ኰረብታ ሠራ።

8 ለአማልክቶቻቸው ዕጣን ለሚያጥኑና መሥዋዕት ለሚያቀርቡ ለሌሎቹ ሚስቶቹም ሁሉ በዚሁ ዐይነት ሠራላቸው።