1 ነገሥት 12:25-31 NASV

25 ከዚያም ኢዮርብዓም በኰረብታው አገር በኤፍሬም የምትገኘውን ሴኬምን ምሽግ አድርጎ ሠራ፤ በዚያም ተቀመጠ። ደግሞም ያንን ትቶ በመውጣት የጵኒኤልንተ ምሽግ ሠራ።

26 ኢዮርብዓም በልቡ እንዲህ ሲል አሰበ፤ “መንግሥቱ ለዳዊት ቤት የሚመለስ ይመስላል፤

27 ይህ ሕዝብ መሥዋዕት ለማቅረብ ኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚወጣ ከሆነ፣ እንደ ገና ልቡን ወደ ጌታው ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሮብዓም ሊያዞር ነው። ከዚያም እኔን ይገድለኛል፤ ወደ ንጉሡም ወደ ሮብዓም ይመለሳል።”

28 ንጉሡ ከመከረበት በኋላ ሁለት የወርቅ ጥጆች አሠርቶ ሕዝቡን፣ “እስራኤል ሆይ፤ ወደ ኢየሩሳሌም እስካሁን የወጣኸው ይበቃል፤ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ እነዚህ ናቸው” አለ።

29 አንዱን በቤቴል ሌላውንም በዳን አቆመው።

30 ይህም አድራጎት ኀጢአት ሆነ፤ ሕዝቡም በዚያ ላለው ለመስገድ እስከ ዳን ድረስ ርቆ ሄደ።

31 ኢዮርብዓም በማምለኪያ ኰረብቶች ላይ አብያተ ጣዖታትን ሠራ፤ ከሕዝቡ የተለያዩ ክፍሎች ሁሉ፣ ሌዋውያን ካልሆኑት ካህናትን ሾመ።