1 ነገሥት 12:27-33 NASV

27 ይህ ሕዝብ መሥዋዕት ለማቅረብ ኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚወጣ ከሆነ፣ እንደ ገና ልቡን ወደ ጌታው ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሮብዓም ሊያዞር ነው። ከዚያም እኔን ይገድለኛል፤ ወደ ንጉሡም ወደ ሮብዓም ይመለሳል።”

28 ንጉሡ ከመከረበት በኋላ ሁለት የወርቅ ጥጆች አሠርቶ ሕዝቡን፣ “እስራኤል ሆይ፤ ወደ ኢየሩሳሌም እስካሁን የወጣኸው ይበቃል፤ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ እነዚህ ናቸው” አለ።

29 አንዱን በቤቴል ሌላውንም በዳን አቆመው።

30 ይህም አድራጎት ኀጢአት ሆነ፤ ሕዝቡም በዚያ ላለው ለመስገድ እስከ ዳን ድረስ ርቆ ሄደ።

31 ኢዮርብዓም በማምለኪያ ኰረብቶች ላይ አብያተ ጣዖታትን ሠራ፤ ከሕዝቡ የተለያዩ ክፍሎች ሁሉ፣ ሌዋውያን ካልሆኑት ካህናትን ሾመ።

32 በይሁዳ እንደሚደረገው ሁሉ እርሱም በስምንተኛው ወር ዐሥራ አምስተኛው ቀን በዓል እንዲሆን ወሰነ፤ በመሠዊያውም ላይ መሥዋዕት አቀረበ። ለሠራቸው ጥጆች መሥዋዕት በማቅረብም እንዲህ ያለውን ድርጊት በቤቴል ፈጸመ። በማምለኪያ ኰረብቶች ላይ ላሠራቸው አብያተ ጣዖታት በቤቴል ካህናቱን መደበ።

33 ራሱ በመረጠው በስምንተኛው ወር፣ በዐሥራ አምስተኛው ቀን በቤቴል ባቆመው መሠዊያ ላይ መሥዋዕት አቀረበ፤ ስለዚህ ለእስራኤላውያን በዓል ወሰነላቸው፤ ዕጣንም ለማቅረብ ወደ መሠዊያው ወጣ።