1 ነገሥት 19:15-21 NASV

15 እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “በመጣህበት መንገድ ተመልሰህ ወደ ደማስቆ ምድረ በዳ ሂድ፤ እዚያ ስትደርስም አዛሄልን በሶርያ ላይ እንዲነግሥ ቅባው።

16 እንዲሁም የናሜሲን ልጅ ኢዩን በእስራኤል ላይ እንዲነግሥ ቅባው፤ ደግሞም ነቢይ ሆኖ በእግርህ እንዲተካ የአቤል ምሖላን ሰው የሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ቅባው።

17 ከአዛሄል ሰይፍ ያመለጠውን ኢዩ ይገድለዋል፤ ከኢዩ ሰይፍ ያመለጠውን ደግሞ ኤልሳዕ ይገድለዋል።

18 እኔም ጒልበታቸው ለበኣል ያልተንበረከከውንና አፋቸው ምስሉን ያልሳመውን ሰባት ሺህ ሰዎች በእስራኤል አስቀራለሁ።”

19 ስለዚህ ኤልያስ ከዚያ ተነሥቶ ሲሄድ የሣፋጥን ልጅ ኤልሳዕን ዐሥራ ሁለት ጥማድ በሬ አውጥቶ ራሱ በዐሥራ ሁለተኛው ጥማድ በሬ ሲያርስ አገኘው። ኤልያስም ወደ እርሱ መጥቶ መጐናጸፊያውን በላዩ ጣለበት።

20 ከዚያም ኤልሳዕ በሬዎቹን ትቶ ኤልያስን ተከትሎ እየሮጠ፣ “አባቴንና እናቴን ስሜ እንድሰናበታቸው ፍቀድልኝ፤ ከዚያም እከተልሃለሁ” አለው።ኤልያስም መልሶ፣ “እኔ ምን ያደረግሁህ ነገር አለ? ልትመለስ ትችላለህ” አለው።

21 ስለዚህም ኤልሳዕ ትቶት ተመለሰ። ሁለቱን በሬዎቹን ወስዶ ዐረደ፤ የዕርሻ ዕቃውን አንድዶ ሥጋቸውን በመቀቀል ለሕዝቡ ሰጠ፤ እነርሱም በሉ። ከዚያም ኤልያስን ለመከተል ሄደ፤ ረዳቱም ሆነ።