1 ነገሥት 2:29-35 NASV

29 ኢዮአብ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ መሄዱንና በመሠዊያው አጠገብ መሆኑን ንጉሥ ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስን፣ “ሂድና ግደለው!” ብሎ አዘዘው።

30 ስለዚህም በናያስ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ገብቶ ኢዮአብን፣ “ንጉሡ፣ ‘ከዚህ ውጣ’ ይልሃል” አለው።እርሱ ግን “አልወጣም፣ እዚሁ እሞታለሁ” አለው።በናያስም፣ “ኢዮአብ የሰጠኝ መልስ ይህ ነው” በማለት ለንጉሡ ተናገረ።

31 ንጉሡም በናያስን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “በል እንዳለው አድርግ፤ ግደልና ቅበረው፤ ኢዮአብ በከንቱ ካፈሰሰው ንጹሕ ደምም እኔንና የአባቴን ቤት አንጻን።

32 አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ኢዮአብ በሁለቱ ሰዎች ላይ አደጋ ጥሎ በሰይፍ ገድሎአቸዋልና ስላፈ ሰሰው ደም እግዚአብሔር ይበቀለዋል። የእስራኤል ሰራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔርና የይሁዳ ሰራዊት አዛዥ የዬቴሩ ልጅ አሜሳይ ሁለቱም ከእርሱ የተሻሉና ይበልጥ ትክክለኛ ሰዎች ነበሩ።

33 የደማቸውም ዕዳ ለዘላለም በኢዮአብና በዘሩ ራስ ላይ ይሁን። ነገር ግን በዳዊትና በዘሩ፣ በቤቱና በዙፋኑ ላይ የእግዚአብሔር ሰላም ለዘላለም ጸንቶ ይኑር።”

34 ስለዚህም የዮዳሄ ልጅ በናያስ ወጣ፤ ኢዮአብንም መቶ ገደለው፤ እርሱም በምድረ በዳ ባለው በገዛ ምድሩ ተቀበረ።

35 ንጉሡም በኢዮአብ ቦታ የዮዳሄን ልጅ በናያስን በሰራዊቱ ላይ ሾመ፤ በአብያታርም ቦታ ካህኑን ሳዶቅን ተካ።