8 “ወደ መሃናይም በሄድሁ ጊዜ፣ ክፉኛ የረገመኝ የባሑሪም ሰው የብንያማዊው የጌራ ልጅ ሳሚ እነሆ፤ ከአንተ ዘንድ ይገኛል፤ ሊቀበለኝ ወደ ዮርዳኖስ ሲወርድ፣ ‘በሰይፍ አልገድልህም’ ብዬ በእግዚአብሔር ስም ምዬለታለሁ፤
9 አሁን ግን በደል እንደሌለበት ሰው አትተወው፤ ጥበበኛ ነህና መደረግ ያለበትን ታውቃለህ፤ ሽበቱን በደም ወደ መቃብር አውርድ።”
10 ከዚያም ዳዊት ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ።
11 ዳዊት በኬብሮን ሰባት ዓመት፣ በኢየሩሳሌም ሠላሳ ሦስት ዓመት ባጠቃላይ አርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ነገሠ።
12 ስለዚህ ሰሎሞን በአባቱ በዳዊት ዙፋን ተቀመጠ፤ መንግሥቱም እጅግ የጸና ሆነ።
13 በዚህ ጊዜ የአጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄደ፤ ቤርሳቤህም፣ “የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው፤እርሱም፣ “አዎን በሰላም ነው” ብሎ መለሰ።
14 ከዚያም፣ “የምነግርሽ ጒዳይ አለኝ” አላት።እርሷም፣ “እሺ ተናገር” ብላ መለሰች።