1 ነገሥት 20:16-22 NASV

16 እነርሱም ቤን ሀዳድና ከእርሱ ጋር ተባብረው የነበሩት ሠላሳ ሁለቱ ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሰክረው ሳለ እኩለ ቀን ላይ መጡ።

17 በግንባር ቀደምትነት የወጡት ግን፣ የየአውራጃው አዛዥ የሆኑት ወጣት መኰንኖች ነበሩ።በዚህ ጊዜ ቤን ሀዳድ ሰላዮች ልኮ ነበርና እነርሱም፣ “ሰዎች ከሰማርያ ወጥተው ወደዚህ በመምጣት ላይ ናቸው” ብለው ነገሩት።

18 እርሱም፣ “አመጣጣቸው ለሰላምም ይሁን ለጦርነት ከነሕይወታቸው ይዛችሁ አምጧቸው” አለ።

19 የየአውራጃው አዛዥ የሆኑ ወጣት መኰንኖችም ሰራዊቱን አስከትለው ከከተማዪቱ ወጡ፤

20 እያንዳንዱም በፊቱ የገጠመውን ጠላት ገደለ፤ ሶርያውያን ሸሹ፤ እስራኤላውያንም ያሳድዷቸው ጀመር። የሶርያ ንጉሥ ቤን ሀዳድ ግን በፈረሱ ላይ ሆኖ ከጥቂት ፈረሰኞቹ ጋር አመለጠ።

21 የእስራኤል ንጉሥ አክዓብም ወደ ፊት በመግፋት ፈረሶችንና ሠረገሎችን ማረከ፤ በሶርያውያንም ላይ ከባድ ጒዳት አደረሰባቸው።

22 ከዚያም በኋላ ነቢዩ ወደ እስራኤል ንጉሥ መጥቶ፣ “በሚመጣው የጸደይ ወራት የሶርያ ንጉሥ ተመልሶ ይመጣብሃልና በርታ፤ ምን ማድረግ እንዳለብህም ዕወቅ” አለው።